
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ተጉዘን ነጭ ጤፍ ከሚታፈስበት እነማይ ወረዳ ዋና ከተማ ቢቸና ደረስን። ያሰብነውን ቦታ ለማየት ጉዟችን ቀጠለ። ከቢቸና ወደ ደቡብ- ምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ሄደን ቁይ ከተባለች ከተማ ደረስን። ቁይ የ”ደባይ ጥላት ግን” ወረዳ ዋና ከተማና
በብዙ ጸጋ የተሞላች ከተማ ናት። ሸንኮራ አገዳ፣ ማንጎ፣ ሙዝ፣ እና ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬዎች የቁይን ገበያ አጥግበውታል። ከገበያ ቅኝታችን ቀጥሎም በደባይ ጥላት ግን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፍሬው ካሴ መሪነት ከከተማዋ ወደ ገጠሩ አካባቢ ተጓዝን።
በዋናነት ማየት የፈለግነው በወረዳው ያለውን የበጋ መስኖ እንቅስቃሴ ነው። የበጋ ስንዴ ልማት በ”ደባይ ጥላት ግን” ወረዳ ሲጀመር የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች ለማለማመድ ያደረጉትን ጥረት አቶ ፍሬው በመንገዳችን ላይ እያወጉን ቀጠልን።
በስንዴ፣ ድንች፣ ባቄላ እና በሌሎችም ሰብሎች የተሸፈነ መሬት እያየን መዳረሻችንን ይጥባቆ ቀበሌ አደረግን። ይጥባቆ በጋ ላይ ኾናም የክረምት መልክ ያላት አረንጓዴ እና ለምለም ቀበሌ ናት። ወሩ ሚያዚያ ቢኾንም በሰፊ ማሳ ላይ በንፋስ ሽውታ የሚዘናፈል የስንዴ ሰብል በይጥባቆ አለ።
ወደ ስንዴው ማሳ ገብተን አርሶ አደሮችን አገኘን። አርሶ አደር ያደርጋል ደምስ የበጋ ስንዴ በስፋት ዘርተዋል። ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ኾነው በስንዴ ማሳቸው ውስጥ በሥራ ላይ ተጠምደው ነው ያገኘናቸው። የስንዴ ሰብላቸው በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አሳይተውናል። የራሳቸውን ፍጆታ ከማረጋገጥ አልፎ ወደ ገበያም የሚቀርብ ውጤት እንደሚያገኙም ነግረውናል።
በ2014 ዓ.ም ስንዴን በመስኖ ለማልማት ከመንግሥት የወረደውን ተግባር በቶሎ መቀበል አዳግቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ድጋፍ ለመስጠት ወደ ቀየው የመጡ የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ አልቀበልም በማለታቸው ግጭት ተፈጥሮ ለእስር ተዳርገው እንደነበርም በቁጭት ተናግረዋል።
“የበጋ ስንዴ እንድዘራ የጠየቁ የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ ባለመቀበሌ ተጸጽቻለሁ” ያሉት አርሶ አደሩ አሁን ላይ ስለበጋ ስንዴ ጥቅም በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ወደፊት በየዓመቱ በበጋ ስንዴ ልማት በመሳተፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመኾን በራሳቸው ተነሳሽነት እንደሚሰሠሩ ገልጸዋል።
የደባይ ጥላት ግን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ፍሬው ካሴ በወረዳው የበጋ ስንዴ ልማት የተጀመረው በ2014 ዓ.ም ነው ብለዋል። አርሶ አደሮች ስንዴን በመስኖ የማልማት የቀደመ ልምድ ስላልነበራቸው ውጣ ውረዶች ገጥመው እንደነበርም አስታውሰዋል። “አርሶ አደሮች ዘላቂ ጥቅም ያገኙ ዘንድ ግንዛቤ ከመፍጠር በተጨማሪ የበጋ ስንዴን ተገደው እንዲዘሩ አድርገን ነበር” ሲሉ ነግረውናል።
አቶ ፍሬው በ2014 ዓ.ም 40 ሽህ 12 ኩንታል ስንዴ ከበጋ ምርት ተገኝቷል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም ለአርሶ አደሮች የተሻለ ግንዛቤ በመፈጠሩ በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች ላይ የበጋ ስንዴ እየለማ መኾኑን አመላክተዋል። በወረዳው 2006 ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ክላስተር መሸፈኑንም ተናግረዋል።
አቶ ፍሬው አሁን ላይ አርሶ አደሮች ከመንግሥት ጉትጎታ ወጥተው በራስ ተነሳሽነት የበጋ ስንዴ እያለሙ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!