“ሊነጋ ሲል ይጨልማል እና ነገን ለማየት ጠንክረን እንሥራ” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)

97

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ አባል በነበሩት አቶ ግርማ የሽጥላን ድንገተኛ ሞት ለመዘከር የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሁሉም መምሪያ ሠራተኞች፣ በብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊና የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ አባል በነበሩት አቶ ግርማ የሽጥላ አሳዛኝ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ለመግለጽ የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

በጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል። በጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ(ዶር) የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል።

ዶክተር ድረስ አቶ ግርማ የሽጥላ የሀገርን አንድነት የሠበኩና የሀገር አንድነትን ለማጽናት ብዙ የለፉ የሀገር ባለውለታ ናቸው ብለዋል። ሊነጋ ሲል ይጨልማል እና ነገን ለማየት ጠንክረን እንሥራ ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳሕሉ (ዶ.ር)።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው “ከመገዳደል ወጥተን ሀሳብን በሀሳብ በመሞገት ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጠንክረን መሥራት አለብን” ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ስድስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች።
Next articleሻሸመኔ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መመለሱን አረጋገጠ።