ከሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ።

99

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ በተከሰቱ  የእርስ በርስ ጦርነቶች  በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ለዚህ ደግሞ ሱዳንን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።

በሱዳን አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነት የመጀመሪያ ሳይሆን  እ.አ.አ ከ1955 እስከ 1972  እና ከ1983 እስከ 2005 በተቀሰቀሱ ሁለት  የእርስ በርስ ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። በተለይም ደግሞ  ለ22 ዓመታት በዘለቀው የሁለተኛው የእርስ በርስ ጦርነት የሁለት ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ የአሁኗን ደቡብ ሱዳንን አዋልዷል።

አሁን ላይ በሱዳን በሁለቱ ጀነራሎች መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ የሱዳንን ሕዝብ መከራ ውስጥ ጥሏል። በዚህ ጦርነት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ከሱዳን እየለቀቁ በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ  ይገኛል።  ከዚህ ውስጥ ደግሞ መሐመድ ሰኢድ አንዱ ነው።  መሐመድ ሰኢድ በሀገረ ሱዳን ካርቱም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እንደኖረ ነግሮናል።

ጦርነቱ  በከተሞች ላይ መካሄዱ ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ የማይታወቅ ጥይት የሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ተመልክቷል። በጦርነቱ የውኃ፣  የመብራት፣ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በመቋረጣቸው  ሞቃታማዋ  የካርቱም ከተማ  ከሰማይ በሚወርደው የአየር እና የጥይት አረር ጋር ተዳምሮ ገሃነም አድርጓታል።  በዚህም ምክንያት በመተማ አድርጎ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ለመግባት መገደዱን ነው የገለጸው።

መሐመድን እንደ አብነት አነሳን እንጂ ሌሎች ተፈናቃዮችም በተቀሰቀሰው ግጭት ጨርቅና ማቄን ሳይሉ በድንገት እንደወጡ ነው የነገሩን።   ከጦርነት አውድማው መውጣታቸው  ትልቅ እፎይታ ቢሰጣቸውም ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በቀይ መስቀል በኩል ከሚደረግ የውኃና የብስኩት ድጋፍ ባለፈ የሚቀርብ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሻምበል ዋለ እንዳሉት  ማኅበሩ  የውኃ፣  የብስኩትና ለምኝታ የሚያገለግል ምንጣፍ  ለተፈናቃዮች  እያቀረበ ይገኛል።

የተጠፋፉ ቤተሰቦችንም በስልክ የማገናኘት ሥራ እየተሠራ ነው።  በቀጣይ ችግሩ እየሰፋ ከሄደ መደረግ ስለሚገባው ጉዳይ ጥናት ተጠንቶ  በዋና ጽሕፈት ቤት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበሩ በየጊዜው ክትትል እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። የበሰለ ምግብ እንዲቀርብም መጠየቁን ነግረውናል።

ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችም መሳተፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች የተሰጠ መግለጫ
Next articleከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ለሚዛን አማን ከተማ አሥተዳደር የ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።