በዩኒቨርሲቲዎች አለመረጋጋቱን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከአቅም በላይ የሆኑ ድርጊቶች መኖራቸው ታውቋል፡፡

199

ከሰሞኑ ግጭት በተነሳባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ውይይቶች ቢደረጉም ስጋቶች አለመቀረፋቸውን ለአብመድ በስልክ አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የተማሪዎቹን ስጋት በሚቀርፍ ደረጃ መፍትሔ አለመስጠታቸውን ነው የነገሩን፡፡
የፀጥታ ችግር ባለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የመከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ የፀጥታ አካላት ገብተው እንዲያረጋጉ መደረጉ ታውቋል፤ ሆኖም ግን የፀጥታ አካላት በየዶርሙ መጠበቅ ስለማይችሉ ስጋት ውስጥ ነን በሚል ተማሪዎቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለተወሰነ ጊዜ እንዲሄዱ እንዲፈቀድላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ጠይቀዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ ደግሞ ሁኔታዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ በመሆናቸውና ተማሪዎቹ ያለአግባብ የትምህርት ጊዜ ማባከን የሌለባቸው መሆኑን በማመላከት ተማሪዎቹ እንዲሄዱ አልፈቀዱም፡፡

ከመደ ዋለቡ ዩኒቨርሲቲ ስለሁኔታው የተናገሩት ተማሪዎች ችግሩ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ በመሆን በፀጥታ አካላት እየተጠበቁ እንዳሉ እና ሁኔታዎች አመች አለመሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አቡበከር ችግሩን ለመፍታት 18 አባላት ያሉት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች እና ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን እያወያዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ችግሩን በመፍታት የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አቡበከር ተናግረዋል፡፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጊምቢ “ካምፓስ” ላይ ትናንት ሕዳር 4/2012 ዓ.ም መጠነኛ ችግር ተፈጥሮ የተወሰኑ ተማሪዎች ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ስለሁኔታው መረጃ ያደረሱን ተማሪዎች ተናግረዋል። የመከላከያ ሠራዊት በመግባቱ ችግሩ ቢበርድም ስጋት ላይ በመሆናቸው በየዶርሙ ተሰባስበው መቀመጣቸውንም ማምሻውን ነግረውናል፡፡

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የጊምቢ “ካምፓስ” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ቀናቴ ነጋሳ እንደተናገሩትም ትናንት ጠዋት በተማሪዎች መመገቢያ አካባቢ ተማሪዎች ድንጋይ በመወራወራቸው የተወሰኑ ችግሮች ቢፈጠሩም ችግሩን በፀጥታ ኃይሉ መቆጣጠር ተችሏል፡፡ ተማሪዎቹ ሠላም አውርደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በአባገዳዎች እና በዩኒቨርሲቲው ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ነግረውናል፡፡ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያረጋገጡልን፡፡

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በፀጥታ ኃይል እየተጠበቁ እንደሆነ እና ሁኔታው ግን አመቺ እንዳልሆነ ነግረውናል፡፡ ተማሪዎቹ እንዳሉት ትናንት ጠዋት አካባቢ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተማሪዎችን ለማነጋገር ሲሞክሩ ለምን ታነጋግራላችሁ ያሉ ተማሪዎች ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ቢሆንም በፀጥታ ኃይሉ ተረጋግቷል፡፡

ተማሪዎቹ በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ቢነግሩንም የዩኒቨርሲቲው አካላት ስልካቸው ባለመሥራቱ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

Previous articleከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለውን መቃቃር ክልሎቹን ከሚመሩትና በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተፍካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ሰብሳቢነት ውይይት አድርገዋል፡፡
Next articleበህዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውኃ ሚኒስትሮች እየተወያዩ ነው።