
ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ግራቅዳምን ቀበሌ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ነው ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የኾነው።
በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ፣ በአመልድ ኢትዮጵያ ጆንስ ሪግ ዋሽ ፕሮጀክትና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በ22 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከ10 ሺህ 5 መቶ በላይ ለሚኾኑ ለግራቅዳምን ታዳጊ ከተማ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ 2 ጥልቅ ጉድጓዶች፣ 19 ቦኖዎችንና 100 ሜትር ኪዩብ የመያዝ አቅም ያለው የውኃ ታንከር ያካተተ ነው። በሰከንድ 50 ሜትር ኪዩብ ውኃ የማመንጨት አቅም አለውም ተብሏል።
የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ለማኅበረሰቡ ሙሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ በፀሐይ የሚሠራ የሶላር ኀይል ፣የመብራት ዝርጋታና ጀኔሪተር የተሟላለት ነው።
የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!