
ሁመራ: ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የአካባቢው ኅብረተሰብ ለበርካታ ዓመታት ነጻነቱን ለመጎናጸፍ መራራ ትግልን አድርጓል። በባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ ሃብት ያለ ከልካይ ሲዘረፍ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ግን ቀየውን ለቆ ሲሰደድ፣ ግፍና መከራን ሲቀበል ቆይቷል።
ተፈጥሮ በቸራቸው ጸጋዎች እንዳይጠቀሙ በወረዳዎችና በከተማ አሥተዳደሮች የመሠረተ ልማት እንዳይስፋፋ የባለፈው ሥርዓት ከፍተኛ ጫና አድርጓል።
ታዲያ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የነጻነቱን ካባ ከተጎናጸፈ ማግስት የልማት ጥማቱን ለመቁረጥ ከሁለት ዓመታት በላይ ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ ቢኾንም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል።
ነዋሪነታቸው በሀገረ አሜሪካ የኾኑት አቶ ማሩ ዓምዶም ከነጻነት ማግሥት የአካባቢውን ኅብረተሰብ የልማት ተነሳሽነት በመመልከት በቃብትያ ሁመራ ወረዳ አዲኸርዲ ከተማ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት በማስገንባት ለኅብረተሰቡ አስረክበዋል።
ዕውቀት የሀገር መሠረት ነው ያሉት አቶ ማሩ በልጃቸው መታሰቢያነት” ዘነበ ማሩ መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍትን” ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማስገንባታቸውን ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድ ነጻነቱን በዕውቀቱ አበልጽጎ ማንነቱን እንዲያስከብር ቤተ መጽሐፍት ዕውቀት ይሸመትበታል ያሉት አቶ ማሩ ከ600 በላይ መጽሐፍትን ፣ ወንበሮችን ፣ የመጽሐፍ መደርደሪያ ሸልፎችንና 5 ኮምፒውተሮችን ማበርከታቸውንም ተናግረዋል ።
በቀጣይ ሌሎች መጽሐፍትንና 25 ኮምፒውተሮችን ለማስገባት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም አንስተዋል።
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአካባቢው ኅብረተሰብ የልማት ተጠቃሚ እንዳልነበር የቃብትያ ሁመራ ወረዳ አሥተዳዳሪ አቶ አታላይ ታፈረ ገልጸዋል። ከነጻነት ማግሥት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በወረዳው እየተከናወኑ መኾኑን ተናግረዋል።
ከነጻነት በፊት በአካባቢው የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት ባለመኖሩ ተማሪዎች የተለያዩ ዕውቀቶችን እንዳይሸምቱ እንቅፋት ኾኗቸው እንደነበር ያነሱት አሥተዳዳሪው የቤተ መጽሐፍቱ መገንባት ትውልድን የሚገነባና ለሀገር ብቁ የኾነ ዜጋን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት በመገንባቱ ደስተኛ መኾናቸውን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸው ቤተ መጽሐፍቱን ተጠቅመው ዕውቀትን ገንዘብ እንዲያደርጉ እገዛና ቁጥጥር እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የሕዝብ ቤተ መጽሐፍቱ በአቶ ማሩና ቤተሰቦቹ በሁለት ወራት ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።
ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!