
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሚያዚያ 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚሰጠው 4ኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ማቀዱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡ ክትባቱ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
በሀገረ ቻይና ሁቤል አውራጃ ውኃን ከተማ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ታኀሣሥ 21/2012 ዓ.ም የዓለም ሕዝብን ጆሮ የሳበ አስደንጋጭ ዜና ተስተጋባ፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ክስተት ኾኖም ተነገረ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ጥር 21/2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የኀብረተሰብ ጤና አደጋ በመኾኑ ሁሉም የዓለም ሕዝብ በይመለከተኛል ስሜት ሊከታተል እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጠ፡፡ መጋቢት 2/2012 ዓ.ም ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ መኾኑ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል በይፋ ታወጀ፡፡
ዓለም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት በምትታመስበት፤ ዓለም አቀፍ የንግድ፣ የቱሪዝም እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባልተለመደ መልኩ በቆመበት በዚያ ጊዜ ሁለት ወራትን ዘግይቶ ቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመድረሱ የአንድ ጃፓናዊ የምርመራ ውጤት አረጋገጠ፡፡ መጋቢት 4/2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመገኘቱ ከደቡብ አፍሪካ የመጣው የምርመራ ውጤት አረጋገጠ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ብቻ የበርካቶችን ሕይዎት ነጥቋል፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መናጋትንም ፈጥሯል፡፡
የቫይረሱን ፈጣን ሥርጭት እና ጉዳት ለመቀነስ ከቀረቡ የመከላከያ መንገዶች መካከል ፍቱን የተባለለት መከላከያ ክትባቱ እንደኾነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ በቅርቡም የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት በኢትዮጵያ ለ4ኛ ዙር ይሰጣል ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች አሥተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት በሰጡት መግለጫ 4ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ከሚያዚያ 28/2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2/2015 ዓ.ም ለተከታታይ ስድስት ቀናት ይሰጣል ብለዋል፡፡ ክትባቱን በክልሉ የሚገኙ እና ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉም ዜጎች ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አሥተባባሪው በክልሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ክትባቱን ለማዳረስ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ክትባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወስዱ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ ወርቅነህ ከዚያ ውጭ የመጀመሪያ ዙር የወሰዱ ሁለተኛ ዙር፤ ሁለተኛ ዙር ወስደው ስድስት ወራት ያለፏቸው ደግሞ የማጠናከሪያ ክትባት እንደሚወስዱ ገልጸዋል፡፡ አሁንም የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ሥጋት ነው ያሉት አሥተባባሪው ክትባቱን መውሰድ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል እስካሁን ድረስ በተሰጡት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶች 11 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ተብሏል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለዓለም ሕዝብ ጆሮ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ686 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከ500 ሺህ 800 በላይ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ ከ7 ሺህ 570 በላይ ዜጎች ደግሞ ሕይዎታቸውን እንዳጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!