ቋሚ የጠቅላይ ሚንስትር ቤተ- ንባብ በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት  ተከፈተ፡፡

118

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተጨማሪም “ታሪክን መሰነድ ለትውልድ” በሚል የመጽሐፍ ዐውደ  ርዕይ ከሚያዚያ 24 እስከ ሚያዝያ 29 በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ተከፍቷል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 6 ቀናት የሚካሔደው ዐውደ ርዕይ ያዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው፡፡

በዚህ የመጽሐፍ ዐውደ ርዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአመራርነት ዘመናቸው ለህትመት ያበቋቸው የህትመት ውጤቶች፣ባለፉት አራት ዓመታት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ያሳተሟቸው ህትመቶች የሚተዋወቁበት  ነው ተብሏል።

ዐውደ ርዕዩ የንባብ ባሕልን ማሳደግ ዓላማ ማድረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ፕረስ ሴክሬታሪያት ቢሌኒ ስዩም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም  ዛሬ የተከፈተው ቋሚ የጠቅላይ ሚንስትር ቤተ ንባብ በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት በየጊዜው ኢትዮጵያን የሚመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የጽሑፍ ሥራዎቻችው እና ታሪኮቻቸው ተሰንደው የሚቀመጡበት ነው ተብሏል።

ቤተ ንባቡን የከፈቱት የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለም ፀሀይ ጳውሎስ ናቸው።

እንደ ፕረስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ ገለጻ ቋሚ ቤተ ንባቡ መሪዎች በሥራ ገበታቸው ኾነው የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ፣ ህትመቶች እና ክንውኖችን አንባቢያን በአንድ ቦታ የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር ነው፤  በዐውደ ርዕዩም መጽሐፍቱ ለሽያጭ ይቀርባሉ ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኀበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው  የዘመኑን ሐሳብ  እና  ድርጊት እየጻፍን በታሪክ ዘርፍ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት  አይነተኛ መፍትሔ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል።

የብሔራዊ ቤተ መጽሐፍት እና መዘክር ኃላፊ ይኩኑ አምላክ መዝገቡ  የታሪክ እና የሌላም የዕውቀት ጉዳይ በተለያየ ቦታ የሚገኝ በመኾኑ የንባብ ጥራት ችግር ይስተዋላል፤  ይህንን ችግር ለመፍታት በአንድ ቦታ መጽሐፍቶቹን ለማሰባሰብ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በጃዊ ወረዳ በተለያዩ ምክንያቶች ጫካ ገብተው የነበሩ ዜጎች እርቅ በመፈፀም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
Next articleከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች የተሰጠ መግለጫ