“ሜይ ዴይ” ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን ጥቅምና መብትን በትግል የማጽናት ተምሳሌት!

181

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የሠራተኞች ቀን ሠራተኛው ለመብቱ ከፍተኛ ትግል ያደረገበት፤ ከሠራተኞች የሥራ ሰዓት ምጣኔ እስከ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ጥበቃ ፤ ለተገቢው ሥራ ተገቢ ክፍያ እስከ ዕኩል ክፍያ መተግበር በትግል የተረጋገጠበት ፣ በመስዋዕትነት የጸና በዓል ነው፡፡

የኢንዱስትሪ አብዮት በአንድ በኩል ባለሃብቶችንና የኢንዱስትሪ አሰሪዎችን በምርታማነት ተጠቃሚ ያደረገበት በሌላ በኩል ግን ሠራተኛውን ለዘርፈ ብዙ በደል እና ብዝበዛ የዳረገበት ክስተት የተፈጠረበት ዘመን ነበር፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ የኢንዱስትሪ መስፋፋት የቀደመውን የሥራ ባሕልና ሁኔታ ቀይሮታልና ሠራተኞች ምቹ ባልኾነ የሥራ ሁኔታ፣ለሥራውም ተመጣጣኝ ባልኾነ ክፍያ፣ከ16 እስከ 20 ስዓታትን እንዲሠሩ ማስገደዱ በሠራተኞች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡

እናም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ላብ አደሮች የሠራተኛው በደልና ጫና ይቁም የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ጥያቄያቸው ግን ተቀባይነት አላገኘም እንዲያውም ከአሰሪዎቻቸው ጋር አቃቃራቸው እንጅ፡፡ ውሎ አድሮም ቢኾን የዩናትድስቴት እና የካናዳ የንግድ እና የሠራተኞች ማሕበራት ፌደሬሽን የሠራተኞችን ጥያቄ አቀጣጠለው፡፡ ከግንቦት 1886 ጀምሮም ሠራተኞች በቀን እስከ 8 ስዓት ብቻ እንዲሰሩ ዓወጀ፡፡

የዓለም አቀፉ ሶሻሊስት ፓርቲ ምክር ቤት በ1889 በፓሪስ ባደረገው ስብሰባው፣የሥራ ሰዓት 8 ስዓት ብቻ እንዲኾን የቀረበውን ሃሳብ ለመደገፍ ግንቦት 1 ቀን 1890 በመላው ዓለም ሰልፍ እንዲደረግ ዓወጀ፡፡ ለዚህ ደግሞ የቀረቡ የሠራተኛውን ጥቅም የሚያስከብሩ ሃሳቦች ከአሠሪውና ከመንግሥትም ሳይቀር ተቃውሞ ማስከተላቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

በተለይም “የሄይማርኬት ሁከት” በመባል በሚታወቀው በችካጎ እ.ኤ.አ የሜይ 1/1886 የሥራ ማቆም እርምጃ በርካታ ሠራተኞች በፖሊሶች በመገደላቸውና “የዓድማ አነሳሽ” የተባሉ መሪዎች በስቅላት በመቀጣታቸው ፣ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የደረሰው ጥቃት በመላው ዓለም ቁጣንና እንቢተኝነትን ቀሰቀሰ፡፡

እ.ኤ.አ በ1889 ፓሪስ ላይ የተጠራው ሁለተኛው የሠራተኞች ኅብረት መሥራች ጉባዔ ሜይ 1 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1890 ጀምሮ የሠራተኞች ቀን “ሜይዴይ” በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

በትግል የጸናው የሠራተኛው የመብትና የጥቅም ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ የሥራ ሰዓት 8 ሰዓት እንዲሆን አድርጓል። ቅዳሜም የረፍት ቀን ኾኗል። ለሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠርን የተመለከቱ አስገዳጅ ሕጎች እንዲወጡም አስችሏል።

በዚህ መሠረትም ሚያዝያ 23 ቀን በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ደግሞ ግንቦት አንድ ቀን የዓለም የሠራተኞች ቀን እየተባለ ለሠራተኞች መብት ሕይወታቸውን የከፈሉ ሰዎች ይታሰቡበታል። የሠራተኞች መብትና ጥቅም እንዲከበር የትግል መነሻነቱም ይዘከርበታል። ለወደፊትም ለሠራተኞች መብትና ጥቅም መታገያ የትግል መስመር ኾኖ በየዓመቱ ይከበራል።

እናም “ሜይ ዴይ” ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን ጥቅምና መብትን በትግል የማጽናት ተምሳሌት በመኾን ተጠቃሽ ነው፡፡ “ሜይ ዴይ” በኢትዮጵያም ለሠራተኛው ጥቅምና የመብት መከበር ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በ2014 ዓ.ም በዓሉን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የ”ሜይ ዴይ” መከበር ዋና ዓላማ ለሠራተኞች መብትና ጥቅም መከበር መስዋዕት የሆኑ ቀደምት ሠራተኞችን በመዘከር ፤ ለቀጣይ የሠራተኛውን የትግል አንድነት ቃል ኪዳን ለማደስም ጭምር እንደሚከበር አብራርቷል፡፡

“ሜይ ዴይ” ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለማችን ከ60 በላይ ሀገራት ብሔራዊ በዓል አድርገው ያከብሩታል፤ ሌሎች ደግሞ ቀኑን አስበውት ይውላሉ።

የዘንድሮው የዓለም የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይ በዓለም ለ134ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለሀገር አካል የኾነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፈቱ::
Next articleከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመስጠት ማቀዱን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡