
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለውን መቃቃር ክልሎቹን ከሚመሩትና በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተፍካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ሰብሳቢነት ውይይት አድርገዋል፡፡
የውይይቱ መካሄድ አንዱ የአንዱን ቁስል በመረዳት እና ሀገርን እና ሕዝብን በማስቀደም በጋራ አጀንዳ ዙሪያ መመካከር እና የረጂምና የአጭር ጊዜ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
ወደፊትም መሰል ውይይቶች እንደሚደረጉ ያመለከቱትት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሁለቱም ክልሎች ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ሕዝቡን ወደ አንድ በማምጣት ለሠላም እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከዚህ በፊት ሁለቱ ድርጅቶች ሲሠሪ የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት ኦዴፓና አዴፓ በማዕከላዊ ኮሚቴ እና ሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ውይይት ማደረጋቸውን አስታውሰው ዛሬ ሕዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ የሁለቱም ክልል ባለሀብቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ውይይት እንዳደረጉና ተቀራርቦ ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ንጉሡ በቀጣይም የሁለቱ ክልሎች ምሁራን ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሁለቱም ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለኢትዮጵያ አንድነት የጋራ አቋም በመያዝ በሀገራዊ ሠላም አስፈላጊነት ላይ አባላቶቻቸውን እና መላ ሕዝቡን ማሳተፍ፣ የሴራ ፖለቲካ ሀገርን እየጎዳ በመሆኑ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የጋራ አቋም መያዝ እና በጉልበት ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ሙከራ በመተው ውይይትን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን