ከ570 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

83

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 15 ዓመት የኾናቸው ከ570 ሺህ በላይ ልጃገረዶች የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዙር የማሕጸን በር ካንሰር ክትባት እንደሚወስዱ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት በሁሉም አካባቢዎች ከሚያዚያ 24/2015 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 27/2015 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት ይሰጣል ነው የተባለው፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ ዛሬ ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት በሰጡት መግለጫ የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ በተለይም በትምህርት ቤቶች በስፋት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የማሕጸን በር ካንሰር ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከፍተኛ ሥርጭት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ ያሉት አሥተባባሪው በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ታላሚዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ ለመጀመሪያ እና ለሁለተኛ  ዙር እንደሚሰጥ ያወሱት አቶ ወርቅነህ ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባቱን የሚወስዱት ልጃገረዶች 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያውን  ዙር ክትባት የወሰዱ ልጃገረዶች አሁን ላይ 15 ዓመት የኾናቸው  ክትባቱን ለሁለተኛ ጊዜ  ይወስዳሉ ብለዋል፡፡

የክትባት ፕሮግራም አሥተባባሪው ክትባቱን ከ570 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ልጃገረዶች ለመስጠት መታቀዱን ገልጸው ዋና የክትባት መስጫ ተቋማት ትምህርት ቤቶች ይኾናሉ ብለዋል፡፡

ክትባቱን በትምህርት ቤቶች ማግኘት የማይችሉ ልጃገረዶች ደግሞ በጤና ተቋማት መውሰድ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ለ4 ዙር የማሕጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባቱ ተሰጥቷል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ  ልጃገረዶች  መከላከያ ክትባቱን እንደወሰዱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሠራተኞችን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው” የሥራና ክህሎት ሚንስቴር
Next articleከ6 ሺህ በላይ የሱዳን ተፈናቃዮች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ገለጸ።