
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሠራተኞችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ለዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም በተለይም ኢትዮጵያን ለማልማት ያላሰለሰ ጥረት ለሚያደርጉ በሁሉም መስክ የተሰማሩ ታታሪ ሠራተኞችን የምናከብርበት እና የምናመሰግንበት ልዩ ቀን ነው ብሏል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት የተደረጉ ጥረቶችን የበለጠ ለማጠናከር በየደረጃው አዳጊ ከሆኑ ፍላጎቶች የሚመነጩ የሠራተኛውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በመንግሥት በኩል ልዩ ልዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ነው ሚንስቴሩ የገለጸው፡፡
ለዚህም ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ መሆኑን ጠቁሞ በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያለው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!