
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሽጥላ የቀብር ሥነ ሥርዓት በትውልድ ሥፍራቸው ሰሜን ሸዋ ዞን መሐል ሜዳ እየከተካሄደ ነው፡፡
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳደሪ መካሻ ዓለማየሁ አቶ ግርማ በጣም ደፋር፣ ፊት ለፊት ተናጋሪ ለአመነበት ሀሳብ የማይታጠፍ ጀግና እና የቁርጥ ቀን ልጅ ነበር ብለዋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብን በታማኝነት እና በቅንነት አገልግሏል፤ ለእኔ ሳይል ለሕዝብ ሲል ኖሯል ነው ያሉት፡፡
ሰሜን ሸዋ ላይ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ አድርጓል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በዞኑ የተሠሩ ፋብሪካዎች ለእርሱ እንደ ሐውልት ቆመው ምስክር ኾነው ይኖራሉ ነው ያሉት፡፡ አብዛኛቹ ፋብሪካዎች በአቶ ግርማ አመራር ዘመን የተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግርማ ከሰው ጋር ተቀራርቦ የመኖር፣ እንደ አማራ ብቻ ሳይኾን እንደ ኢትዮጵያ በአንድነት፣ በትብበርና በወንድማማችነት ስሜት የዚህ ሀገር ችግር መፈታት አለበት ብሎ የሚያምን፣ የአማራ ችግር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ኾኖ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር መፈታት ይችላሉ ብሎ የሚሠራ ነበርም ብለዋል፡፡
ግርማ ሌት ተቀን የሚሠራ ለሰው ልጅች ሁሉ ቅን የሚያስብ ነውም ብለዋል ዋና አሥተዳደሪው፡፡
አስተዋይና በሳል፣ ሀሳቡ ተቀድቶ የማያልቅ፣ በሰሜን ሸዋ ያሉ መሪዎችን ኮትኩቶ ለወግ ለማዕረግ ያበቃ፣ በአማራ ክልል ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣ ነው ብለዋል፡፡ ግርማን የገደሉት ሰዎች አያውቁትም ያሉት ዋና አሥተዳደሪው ግርማ ለሰው የሚያዝን፣ የሰው ልጆች ሁሉ ተዋድደውና ተከባብረው ይኑሩ የሚል ጽኑ አቋም ያለው ነው ብለዋል፡፡
ግርማን አልተረዱትምና በሀሳብ ሞግተው ማሸነፍ ሲችሉ ውድ ልጃችን ነጠቁን ነው ያሉት፡፡ ሥርዓተ ቀብሩ ላይ ተናድደን እና አልቅሰን መለያየት ሳይሆን ግርማ ለተሰዋለት አላማ እስከመጨረሻው ድረስ ውስጣዊ አንድነትን አጠናክረን ዳር ማድረስ አለብን ብለዋል፡፡የአቶ ግርማ ሀሳብ የሚሞት ሳይሆን ክልልና ሀገርን የሚቀይር አንድነትን የሚያመጣ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በውይይት የማይፈታ ነገር የለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ሁሉንም በሰከነ መንገድ ማየትና መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ቤተሰቦቹ እንዳይቸገሩ መደገፍና መንከባከብ ይገባናልም ብለዋል፡፡
ከአቶ ግርማ ጋር የተሰዉ የጸጥታ አካላትን ቤሰተቦች ማሰብና መንከባከብ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን ለቤተሰቦቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!