“የድንበር አልባው መሪ የማይሞተው ሃሳባቸው ለቀሪ ወንድሞቻቸው የሚተርፍ እርሾ ነው” ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ

90

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከወረዳ ባለሙያ እስከ ክልል ከፍተኛ መሪነት የደረሱ፡፡ በፈተና ዘመን የመሻገሪያ ሃሳብ ባለቤት የነበሩ፡፡ በሃሳብ ልዕልና የሚያምኑ እና የተለየ የሃሳብ ልዩነት ያላቸውን የሚያስቀድሙ ተራማጅ መሪ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡

ደፋር፣ ግልጽ፣ የመርሕ ሰው፣ ታጋሽ እና አንደበተ ርትዑነት የሥራ ከባቢያቸው መለያ ሲኾን ተግባቢ፣ ተጫዋች፣ ሰብዓዊነትን የሚያስቀድሙ እና ለዛ ያለው ቀልድ አዋቂነት ደግሞ ከሥራ ጊዜያቸው በስተጀርባ ያለ ማኅበራዊ ማንነታቸው ነበር ይባላል፡፡

ከሽዋ ምድር መሀል ሜዳ እስከ መሀል ሀገር በደረሰው የትምህርት፣ የሥራ እና የኅላፊነት ሥምሪቶቻቸው በርካታ ሰብዓዊ ጥሪቶችን እንዳተረፉ የሚነገርላቸው አቶ ግርማ በህልፈታቸው ማግስት፤ በሽኝታቸው እለት እነዚህ ሰብዓዊ ጥሪቶቻቸው የኾኑ የሥራ እና የማኅበራዊ ሕይወት ባልደረቦቻቸው ማንነታቸውን በእምባ ጭምር ነግረውናል፡፡ ዕውቁ የጥበብ ሰው ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ ደግሞ አቶ ግርማ የሽጥላን “ባለግርማ ወንድም ጥላ” ሲል ነበር የገለጻቸው፡፡

በአመራርነት ዘመናቸው “መንገዶቻችን ቢለያዩም የምንሠራው ለአንድ ሕዝብ እና አንድ ሀገር ነው” ማለትን ያዘወትሩ እንደነበር የሚነገርላቸው የአማራ ክልል ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኅላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሽጥላ ከትግል ጓዶቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው የተነገረላቸውም ሰብዓዊነትን የሚያስቀድሙ እና ኢትዮጵያን ለማጽናት ድንበር አልባ መሪ እንደነበሩ ነው፡፡

በሕይወት ዘመናቸው፤ በአመራርነት ጊዜያቸው “ፈታኝ ዘመን አይበገሬ ትውልድ ይፈጥራል” የሚል በሳል አስተሳሰብን ያነበሩት አቶ ግርማ ችግሮችን በብስለት ለመሻገር፣ ፈተናን በጽናት ለመቋቋም እና ልዩነትን በድፍረት ለመቀበል ያላቸው ቁርጠኝነት በመጨረሻ ዘመናቸው እንኳን አብሯቸው ነበር ይላሉ የትግል ወንድሞቻቸው፡፡ “ጀግና ከመከራ ይወለዳል” በሚለው ጀግኖ በሚያጀግን አስተሳሰባቸው እንደጸኑ በመከራ ውስጥ አልፈው እና ተመላልሰው ሕዝብ፣ መንግሥት እና ሀገር የሰጣቸውን ኅላፊነት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ በጽናት ተወጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል፣ የተለያዩ ተቋማት የሥራ አመራር ቦርድ ኅላፊ እና አባል የነበሩት አቶ ግርማ የአማራ ሕዝብ ከነበረበት የህልውና ሥጋት ፋታ እንዲያገኝ በሳል አመራር የሰጡ፣ በተግባር ተፈትነው የበቁ እና ተናግረው ማሳመንን የተካኑ ምክንያታዊ እና አንደበተ ርቱዕ እንደነበሩ በአስከሬን ሽኝታቸው ላይ ተነስቷል፡፡

ድምበር አልባው መሪ ሩቅ ሕልማቸውን፣ ታላቅ ራዕያቸውን ሳይጨርሱ መንገዳቸው በአጭር ቢቋጩም የማይሞተው ሃሳባቸው ለቀሪ ወንድሞቻቸው የሚተርፍ እርሾ ይኾናል ብለዋል፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁልጊዜም ሀገር የምትገነባው በሚሠሩና በሚሰዉ ልጆቿ ነው” ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
Next article“ግርማን አልተረዱትምና በሐሳብ ሞግተው ማሸነፍ ሲችሉ ውድ ልጃችንን ነጠቁን” አቶ መካሻ ዓለማየሁ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ