
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሽጥላ አስከሬን ሽኝት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል፡፡ በሽኝቱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡
በሽኝት ፕሮግራሙ ንግግር ያደረጉት የአቶ ግርማ የሽጥላ ወንድም አቶ ኃይሌ የሽጥላ ወንድማቸው ተጫዋች፣ ተግባቢ፣ ቅን፣ በቤተሰባቸውና በቤተ ዘመዱ ተወዳጅ፤ ሰው አክባሪና ሩህሩህ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ አባታችን ከተለየን ወዲህ ቤተሰቡን የመምራትና የማሥተዳደር ድርብ ኃላፊነት የተሸከሙ አለኝታችንና ጋሻችን ነበሩም ብለዋል፡፡
ቤተሰቡን ከማሥተዳደር ጎን ለጎን በተለያዩ ተቋማት መንግሥትና ሕዝብን ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ሲተጉና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሠሩ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ሳይኖሩ፣ ሳያዳሉ ራሳቸውን ለሕዝብ አሳልፈው የሰጡ እውነተኛ የሕዝብ ልጅ ነበሩ ነው ያሉት፡፡
ለሀገርና ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት በመንግሥት ሥራ ላይ እያሉ ባላሰብነው እና ባልጠበቅነው ሁኔታ ሩቅ አሳቢ የነበረው ወንድማችንን በአጭሩ ቀጭተውብናልም ብለዋል፡፡ መሪር የኾነ ሀዘን ደርሶብናልም ነው ያሉት፡፡
ከጥቃቱ በኋላ ሕይወታቸውን ማትረፍ ባይቻልም ለተደረገው ርብርብ ምሥጋና እናቀርባለንም ነው ያሉት፡፡ በክብር እንዲሸኝ ስላደረጋችሁም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ የወንድማችን ገዳዮች መንግሥትና ሕዝብ በመረባረብ ለፍርድ እንዲያቀርቡልን እንጠይቃለን ነው ያሉት፡፡ አቅመ ደካማ እናቱን እና ሕጻናት ልጆቹን በትኖ የሞተ በመኾኑ የመንግሥትና የሕዝብ ድጋፍ እንዳይለይን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!