“መላው ሕዝባችን እንዲያውቀው የምንፈልገው ጽንፈኝነት ራሱን በልቶ የሚጨርስ መኾኑን ከሰኔ 15 እና ከሚያዚያ 19 መማር እንደሚቻል ነው” ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

100

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ የደረሰው ግድያ ለሕዝቡና መሪዎች እጅግ አስደንጋጭ፣ መራርና ልብ ሰባሪ ኾኗል ብለዋል፡፡
በተከታታይ በመሪዎች ላይ የሚደረገው ግድያ የአማራን ሕዝብ ስቃይና መከራ ለማስቀጠል በሚሠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ቀጣይነት ያለው መኾኑ ማሳያ ነው፡፡ በሕዝቡ ስም በሚምሉ፣ እንቆረቆራለን በሚሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ከውጭና ከውስጥ በሚሠሩት የተመጋገበ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ መኾኑ ሲታይ ሀዘኑንና ቁጭቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ጽንፈኝነት በወለደው አስተሳሰብ ሰኔ 15 ብርቅና ድንቅ መሪዎቻችንን በሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡ መኾናቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነውም ብለዋል፡፡ ከዚህ አስነዋሪና አሳፋሪ ድርጊት ከወለደው ሀዘን ላይ እያለን ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ያለፍን መኾኑ የሚታወቅ ነውም ብለዋል፡፡

በተከታታይ በሕዝባችን ላይ በደረሰው ሀዘን እና ችግር ሳንወጣና፣ ሳናገግም በማያቋርጥ መንገድ በሚነሳ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የአማራ መሪዎችን በማጥፋት ችግር ሁሉ ይፈታል በሚል ራስን በራስ በማጥፋት የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በሕቡዕ እና በግላጭ የተደራጁ ጽንፈኞች ተከታታይ ጥቃት እየፈጸሙ ነውም ብለዋል፡፡

መላው ሕዝባችን እንዲያውቀው የምንነግረው ጽንፈኝነት ራሱን በልቶ የሚጨርስ መኾኑን ከሰኔ 15 እና ከሚያዚያ 19 መማር እንደሚቻል ነው፡፡ ጽንፈኝነት በአማራ ክልል ላይ የተቃጣ አደገኛ የመከራ በትር ነው፤ የአማራ ክልልን የጦር አውድማ በማድረግ የክልሉን ሰላም የሚነጥቅ ነውም ብለዋል፡፡ ጽንፈኝነት የአማራ ክልል ሕዝብን ወዳጅ አልባ በማድረግ ያነሳቸው ጥያቄዎች በሁሉም ተባባሪነት እንዳይመለሱ የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ጽንፈኝነት ሕዝብን በመከፋፈል ፣እርስ በእርስ በመገዳደል በሕዝባችን ላይ ተስፋ መቆረጥን እና የተሸናፊነትን ሥነ ልቦናን በመገንባት የሚጠናቀቅ እንጂ ለድል የሚበቃ አይደለም ብለዋል፡፡ ጽንፈኝነት ሕዝብን በማዳከም የጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ እንጂ ለድል የሚያበቃ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የተጀመረውን ልማት የሚያቋርጥ፣ የሚያወድም እና የሕዝብን ተስፋ የሚያጨልም መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሕዝቡ አስነዋሪ፣ አሳፋሪና አዋራጅ ድርጊትን በማውገዝ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጠይቀዋል፡፡

ሀዘኑ ተጠናክረን ለጋራ አንድነታችን እንድንነሳ የሚያደርገን እንጂ ወደ ኋላ የሚመልሰን አይደለም ብለዋል፡፡ አንድነታችን አጠናክረን ትግላችን እንድንቀጥል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሕዝቡ በለመደው ታጋሽነቱና ጥበቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላሙን እንዲያስከብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአቶ ግርማ መስዋዕትነት የሚያስተምረው መጽናት አስፈላጊ መኾኑን ነውም ብለዋል፡፡ የጀመርነውን ክልልና ሀገር የማልማት ሥራ አደራ የሚያስቀምጥ ነውም ብለዋል፡፡ ቃል ኪዳናችንን በማደስ ለበለጠ ድልና ትግል እንድንነሳ ጥሪ አቅርባለሁ ነው ያሉት፡፡ አቶ ግርማ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይሉ የታገሉ፣ ያታገሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ናቸውም ብለዋል፡፡

አቶ ግርማ የኖሩት ለሕዝብ ሥራ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ሙሉ ዘመናቸውን ያሳለፉት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው በመድከም ነውም ብለዋል፡፡ ሀዘኑን በአዲስ ቃል ኪዳን በመለወጥ ዳር እናደርሳንም ነው ያሉት፡፡ ሁላችንም የያዝነውን ዓላማ ለማሳካት እስከ መስዋአትነት ቆርጠን መሄድ ግድ እንደሚል ሀዘኑ ያስተምረናልም ብለዋል፡፡ ሀዘናቸውን ላጽናኗቸውም ርእሰ መሥተዳድሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአቶ ግርማ መስዋዕትነት ሀዘን እና ድንጋጤ ቢፈጥርም ዓላማውን ለማሳካት እና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት አምርረን እንተጋላለንም ብለዋል፡፡

ሁላችንም ቤተሰቦቹን እና ልጆቹን እንከባከባለን፣ ተገቢውን ድጋፍም እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡ ወንድሜ ግርማ ጎበዝ ነበርክ፣ ታጋይ ነበርክ፤ ተጫዋችና ተግባቢ ነበርክ፣ አንደበተ ርቱእ ነበርክ፣ ሃሳብ አፍላቂ ነበርክ፣ የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት ያለምንም ማመንታት የምትፈጽም ብርቅ አመራራችን ነበርክ፣ አንተን ማጣት ለእኛ በጣም ከባድ ነው፣ ግን ምን እናደርጋለን፣ ማድረግ የምንችለው ዓላማውን ይዘን ዳር በማድረስ፣ሕዝባችን የሚጎዳውን ጽንፈኝነት አምርረን በመታገል ሁሉም ነገር በሰላምና በውይይት የሚፈታበትን ሀገር መመስረትና መታጋል ብቻ ነው፣ ይህን ለማድረግ እኛ ጓደኞችህ ቃላችንን እናድሳለን ብለዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግርማ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና የአማራን ሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት በሚገባ ያወቀ በሳል መሪ ነበር” አቶ አደም ፋራህ
Next article“ሞት በእውነተኛ ሰዎች ላይ እንጅ በእውነት ላይ ስልጣን የለውም” አቶ ግርማ የሽጥላ