
አዴፓ የሚዋሐድ ከሆነ የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያለውን ግልጽ አቋም መተግበር በሚችልበት መልኩ ውሕደቱን መፈጸም አለበት፡፡
የኢሕአዴግ ሰሞነኛ ፖለቲካዊ አጀንዳ የፓርቲዎች ውሕደት ጉዳይ ሆኖ በማኅበረሰብ አንቂዎችና ፖለቲከኞች እየተነሳ ነው፡፡ ውሕደቱ ‹‹አጋር እና እህት ድርጅቶች ተጣምረው፣ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ በማረጋገጥ ግንባሩ በተጓዘባቸው የመሪነት ጊዜያት የተስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረታቸው ይፈታሉ‹‹ ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ‹ውሕደቱ በአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ምን አንድምታ ይዞ ይመጣል?› ሲል አብመድ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡
የወሰን ይገባኛል እና የማንነት፣ በፍትሐዊነት የመልማት፣ ፍትሐዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ተሳትፎ፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ ከክልሉ ውጭ ያሉ የአማራ ተወላጆች ውክልና አና ሌሎች የኅልውና ጥያቄዎች በአማራ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲነሱ የነበሩ ነገር ግን ምላሽ ያላገኙ ናቸው፡፡ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎችም የክልሉ መሪ ፓርቲ አዴፓ በባለቤትነት ወስዶ የፖለቲካ መታገያው አድርጎ እየሠራባቸው እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች አስታውቋል፡፡
ያነጋገርናቸው ምሁራን አዴፓ የውሕድ ፓርቲው አካል ቢሆን በጥያቄው ተፈጻሚነት ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ በስፋት የሚነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎችን በውሕድ ፓርቲው ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከር እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው አዴፓ የአማራን ሕዝብ ወክሎ እየተንቀሳቀሰ ያለ ፓርቲ እስከሆነ ድረስ ውሕደት በሚያደርግበት ጊዜ የአማራውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ወደ ጎን ትቶ ለድርድር ይቀርባል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡ ሕገ መንግሥት ማሻሻያን ጨምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ የተሠሩትን ትርክቶች ለማስተካከል፣ በማንነቱ ተከብሮ እንዲኖር እና ሌሎች የኅልውና ጥያቄዎችንም በተሻለ መልኩ መመለስ በሚያስችልበት አግባብ እንደሚዋሐድም እምነት አላቸው፡፡ እንደ አቶ መላኩ ገለጻ ውሕደት እና አብሮ መኖር እሴቱ አድርጎት ለዘመናት የኖረበት በመሆኑ ለአማራ ሕዝብ እንደ አዲስ መስበክ አያስፈልገውም፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ለሚያነሳው መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ከሆነ በውሕደቱ ላይ ተቃውሞ ሊኖረው እንደማይችልም ይገምታሉ፡፡ አቶ መላኩ ‹‹በኢትዮጵያዊነት አብሮ ለመቀጠል ግን መስተካከል ያለባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ቅድሚያ መመለስ አለባቸው›› ብለዋል፡፡
‹‹ስለውሕደት እየተወራ ስለማንነት እና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ማንሳት ለምን አስፈለገ?›› ለሚሉ አካላትም ውሕደቱ የፓርቲዎች እንጂ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓቱ ላይ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት እና የክልሎች አወቃቀር እና ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ እስካልተደረገበት ድረስ ጥያቄዎቹ አስፈላጊ እና ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በተለይ የማንነት እና የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በአማራ ክልል ከሚደርሰው ተፅዕኖ አንጻር ጎልቶ ስለወጣ እንጂ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡
አቶ መላኩ የአማራ ክልል ሕዝብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከጥንት እስካሁን መሰዋዕትነት እየከፈለ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ውሕደቱ ምንም ይሁን ምን የሕዝቡ የጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ሕዝቡ ጥያቄውን ማንሳቱን እንደሚቀጥል፤ የሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙም ሕዝቡ ተደራጅቶ በጽናት መታገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ትዕዛዙ አያሌው በበኩላቸው ‹‹ፓርቲዎች በምን መልኩ ይዋሐዳሉ?›› የሚለው ጉዳይ ግልጽነት የሌለው በመሆኑ ለመተንበይ እንደሚያዳግት ተናግረው ውሕደቱ በአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ሊኖር እንደማይችል አመላክተዋል፡፡ ውሕደቱ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል›› ተብሎ የታመነበት በመሆኑ የአማራን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያንን ጥያቄ እንደሚመልስም እምነት አላቸው፡፡ የክልሉ መሪ ፓርቲ አዴፓ ግን የፖለቲካ መታገያው አድርጎ ያያዛቸውን የሕዝብ መሠረታዊ እና የሕልውና ጥያቄዎችን የውሕደቱ አካል አድርጎ መሥራት እንደሚገባው አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡
ከመነሻው አግላይ ሥሪት የነበረው ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም በተጓዘበት መንገድ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ውሕደት ማሰቡ በመልካም ጎኑ የሚታይ ቢሆንም የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ውሕደቱ ብቻ በቂ ሊሆን እንደማይችልም አስረድተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ከመንግሥት አወቃቀሩ፣ ከፌዴራሊዝም አተገባበሩ አና ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው በመሆኑ ማስተካከያው በነዚህ አውዶች ላይም ሊተገበር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ጥያቄዎቹም ምላሽ እንዲያገኙ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ቅድሚያ መንስኤያቸውን ለይቶ ማስተካከያ መውሰድ አለበት፡፡ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ በተደጋጋሚ በተሀድሶ እና በለውጥ ስም አማራ ጠል ትርክቶችን በሕጋዊ ማዕቀፍ በማካተት ኢትዮጵያዊነትን ማደብዘዙንም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የክልሉ መሪ ድርጅት አዴፓ የውሕደቱ አካል የሚሆን ከሆነ የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያለውን ግልጽ አቋም መተግበር በሚችልበት መልኩ ውሕደቱን መፈጸም እንደሚኖርበትም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ