
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሽጥላ የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር መስዋዕትነታቸውን እና ኅላፊነታቸውን በሚመጥን መልኩ በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የትግል አጋሮቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የሽኝት መልዕክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከወንድማችን መስዋዕትነት ዛሬም ለኢትዮጵያ ሰላም በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለብን ተምረናል ብለዋል፡፡
ድርጊቱ ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው ያሉት አቶ አደም ሃሳብን የሚፈሩ፣ ልዩነትን ማስተናገድ የማይችሉ እና የኢትዮጵያ መከራን ማራዘም የሚፈልጉ ኅይሎች መለያ ነው ብለዋል፡፡
ወንድም ግርማ ሰብዓዊነትን የተላበሰ የተግባር እና የመርህ መሪ እንደነበር ያነሱት አቶ አደም “ሀገራዊ ራዕይን የሰነቀ በሳል እና ንቁ የሕዝብ አገልጋይ” ሲሉ ግልጸውታል፡፡
“ግርማ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና የአማራን ሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት በሚገባ ያወቀ በሳል መሪ ነበር” ያሉት አቶ አደም ፋራህ ጉዞውን በአጭር የቀጩ ኅይሎች ሥርዓት አልበኝነትን በማስፈን የግል እና የቡድን ፍላጎትን ለማሳካት የሚሹ ናቸው ብለዋል፡፡
ገዳዮችን ተከታትሎ ለሕግ ማቅረብ እና ሥርዓት ማስፈን የቀጣይ ጊዜ ሥራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!