
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሽጥላ የአስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ወደጅነት ፓርክ እየተካሄደ ነው፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የሽኝት መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ግርማ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን መሪ ነበር ብለዋል፡፡
ከግርማ ጋር በሥራ ምክንያት ከተዋወቅንበት ጊዜ ጀምሮ የተረዳሁት ከራሱ በላይ ለጓደኞቹ የሚያስብ የትግል አጋር መሆኑን ነው ያሉት አቶ ፈቃዱ ግርማ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብሎ የሚያምን መሪ ነበርም ብለዋል፡፡
ታላቅ፣ ተፈሪ እና የተከበረች ኢትዮጵያን የመፍጠር ጉጉት እና ምኞት ነበረው ያሉት አቶ ፈቃዱ “ግርማ በትጋታችን እና በጽናታችን ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን ብሎ የሚያምን መሪ ነበር” ብለዋል፡፡
ግርማ ችግሮች በውይይት ይፈታሉ ብሎ የሚያምን፣ በብስለት የሚሰራ እና ከስሜት የራቀ ወንድም ነበር ያሉት አቶ ፈቃዱ ግርማ ሀገር፣ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ያለፈ መሪ በመሆኑ በጀግንነቱ እና በድፍረቱ እንኮራለን ነው ያሉት፡፡ በመጨረሻም ግርማ እስከ ሞት ድረስ የቆመለትን ዓላማ ዳር ለማድረስ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!