“ማንኛውንም ሐሳብ ፊት ለፊት የሚሟገቱ፣ ፊት ለፊት የሚሟገቱትን እድል የሚሰጡ መሪ ነበሩ” ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)

87

ባሕርዳር : ሚያዝያ 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሽጥላ አስከሬን ሽኝት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡ በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) አቶ ግርማ ሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችሉ፣ ሩህሩህ፣ ለሰው ልጆች ቅን የሚያስቡ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ሁልጊዜም ደግ ነገር የሚያስቡ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡

ማንኛውንም ሐሳብ ፊት ለፊት የሚሟገቱ፣ ፊት ለፊት የሚሟገቱትን እድል የሚሰጡ፣ በሐሳብ የበላይነት በእጅጉ የሚያምኑ፣ ማንኛውም ሃሳብ በሀሳብ የበላይነት መመራት አለበት ብለው የሚያምኑ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ኾኖ፣ ተፈቃቅደውና እኩል ኾነው፣ ኢትዮጵያ አንድ ኾና እንድትቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ነበሩም ብለዋቸዋል፡፡

አስቀድመው የተሸነፉና ማሸነፍ የማይችሉ፣ በኹከት፣ በብጥብጥና በመግደል ማሸነፍ የሚሞክሩ ሰዎች እንዳሉ እያወቁ፣ እንደሚሞቱም ተረድተው፣ በዓላማቸው ጸንተው፣ ከዓላማቸው አንድም ቀን ሳያፈገፍጉ የታገሉ ቆራጥ የሕዝብ ልጅ ናቸውም ብለዋል፡፡

ግርማ መስዋዕት ኾነን የኢትዮያን አንድነት እናጸናለን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እንመሠርታለን በማለት ታግለዋል፣ አታግለዋል ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል የነበረው ውስብስብ ችግር እንዲፈታ፣ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም፣ ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲጋፈጡ በትጋት ሠርተዋልም ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል በርካታ ችግሮችን በመቅረፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋልም ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ችግር ወደ ባሰ ችግር እንዳይገባ እና የአማራ ችግር የሚፈታው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመተባበር ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡ የጎህ ቃል ኪዳን የሚል አዲስ ሃሳብ አምጥተው ሲታገሉ የነበሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማ ወደ ተወለዱበት አካባቢ ሲሄዱ ቀድመው የሚፎክሩለት መኖራቸውን ሳያውቁ ቀርተው ሳይኾን ሞትን በመሸሽ ሕዝቤን አልከዳም፣ ሕዝቤ ጋር ኾኜ ማንኛውንም መስዋዕትነት እቀበላለሁ፣ እየሞትን የሕዝባችን ብልጽግና ይረጋገጣል ብለው ወደ መስዋዕትነት የሄዱ ናቸውም ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ነጋዴዎች አደብ እንዲይዙ እና በሀሳብ ብቻ እንዲሞግቱ ብርቱ ትግል ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሁላችንም እንደ ግርማ እስከምንሞት ድረስ ለሕዝባችን ሌት ተቀን እንሠራለንም ብለዋል፡፡ ከሕዝባቸው ጎን የማይለዩ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

ግርማ የተሰውት ለሕዝብ ነው፣ ልጆቼን አላሉም፣ ልጆቼ ከአማራ ሕዝብ አይበልጡም ብለው ፊት ለፊት የተጋፈጡ ናቸውም ብለዋል፡፡ ከአቶ ግርማ ልጆች ጎን እንቆማለንም ብለዋል፡፡ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግርማ ሕዝብን ለማገልገል ድንበር የማያውቅ መሪ ነበር” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next article“ግርማ በትጋታችን እና በጽናታችን ታላቋን ኢትዮጵያ መፍጠር እንችላለን ብሎ የሚያምን መሪ ነበር” የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ፈቃዱ ተሰማ