
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሽጥላ በደብረ ብርሃን ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር፡፡
ይሄም ቆይታቸው ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡት የመጨረሻው ንግግራቸው ሆኗል፡፡ በቆይታቸውም ስለ ደብረ ብርሃን ከተማ የተመለከቱትን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
➨ቆመን ላናያቸው እንችላለን እንጂ ሕልማችን ደብረ ብርሃን የአየር መንገድ ያላት ከተማ እንድትሆን ነው።
➨ደብረ ብርሃን ከተማ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ከተማ እየሆነች ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በብዛትም ወደ ምርት በመግባትም በኩል ከፍተኛ ፍጥነት ተመልክቻለሁ፡፡
➨ከተማዋ በብዙ መንገድ በመሠረተ ልማት የተጎዳች ናት፡፡ የአስፋልት መንገድ እና የውስጥ ለውስጥ መንገዱም ከተማዋ ከምትጠይቀው እና ከመጣላት የኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን አልነበረም፡፡ አሁን ሰፊ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተሠሩባት አግኝቻለሁ፡፡
➨ደብረ ብርሃን ዪኒቨርሲቲ ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሰጠው ትኩረት በቀጥታ ማኅበረሰቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ታላላቅ ሥራዎችን ሲሠራ ተመልክቻለሁ፡፡
➨ቀደም ሲል በልማት ሥራዎች ላይ ተጀምሮ መቋረጥ፣ ተጀምሮ መጓተት እና በታሰበለት ጥራት ልክ አለመጠናቀቅ ችግሮችን ተመልክቼ ነበር፤ አሁን እነዚህ ችግሮች የተወገዱ በሚመስል መልኩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት በተያዘላቸው ጊዜ እየሄዱ መሆናቸውን ተመልክቻለሁ ብለው ነበር፡፡
➨ከደብረ ብርሃን ባሻገር ለክልላችንም ለሀገራችንም አርዓያ የሚሆን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥራ በከተማዋ እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ድንቅ ሥራ ነው፡፡ ለደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የተገነባው ቴክኖሎጂ ለሚቀጥሉት ከሠላሳ እስከ አርባ ዓመታት የሚሆን ነው፡፡ ይህም የሕዝቡን ቅሬታ የፈታ ነው።
➨በከተማዋ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ የከተማዋ ሕዝብ ዕድለኛ ነው፤ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ፡፡
➨የዓለም አቀፍ መዳረሻ በመሆኗ ምክንያት ይህች ከተማ ሊሠራላት የሚገባው መዋቅራዊ ፕላንም ይሁን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከከተማዋ መሪዎች ባሻገር የክልሉን የዕለት ከዕለት ክትትል ይጠይቃል ብለው ነበር፡፡
➨ከተማዋ እስካሁን ለነዋሪዎቿ እና ለአልሚዎቿ የተመቸች እንድትሆን የክልሉ መንግሥት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት ወደፊትም የሚሰጠውን ትኩረት ይቀጥላል፡፡
➨ወሳኝ የልማት አካባቢዎች ከምንላቸው ቦታዎች መካከል ደብረ ብርሃን አንዷ ናት፡፡ ደብረ ብርሃን የራሷን ልማት ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ልማት ይዛ የምትወጣ በመሆኑ ደብረ ብርሃን ላይ የምንሠራው ሥራ ደብረ ብርሃን ዙሪያ ላሉ አርሶ አደሮችም ልዩ ትርጉም አለው፡፡
➨በኅበረተሰቡ የነበረው ምሬት እየተፈታ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በከተማዋ የሚመጡ ለውጦችን ራሱ እየጠበቃቸው ነው፡፡
➨በአማራ ክልል እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የአማራ ክልል መሪ በሆደ ሰፊነት፣ በብልህነት፣ ከሁሉም በላይ በትዕግሥት እና በውይይት ለመፍታት ሥራዎች እየተከናዎኑ ነው፣ ውጤቶችም እየታዩ ነው፣ የበለጠ ሥራዎች ግን ይጠበቁብናል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
➨ከመሪዎች የሚጠበቀው በጽናት የሚፈለገውን መስዋዕትነት በመክፈል አስተማማኝ ሰላም፣ ፈጣን ልማት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡
➨አመጽና ኃይል ለፍተን ጥረን በብዙ ዓመታት የሠራናቸውን የሚያጠፋ መሆኑን ማስተማር ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል ሲሉም አሳስበው ነበር፡፡
➨ደብረ ብርሃንን እንደ ስሟ የብርሃን ከተማ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ከኅብረተሰቡ ይጠበቃል፤ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቀርባለሁ፤ የክልሉ መንግሥትም ከጎኑ ነው።
አቶ ግርማ የሽጥላ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ቃለ ምልልስ የተወሰደ ።