
በዛሬው እለት ወንድማችን አቶ ግርማ የሺጥላ በሥራ ላይ በነበረበት በታጠቁ ኃይሎች ግድያ ተፈጽሞበታል። እንዲህ አይነት እብሪተኝነት ውድቀትን እንጅ ድልን አያጎናጽፍም። ጥፋትን እንጅ ሰላምን አይሰጥም።
የሕዝባችን የቆየ መገለጫው ሥርዓታዊነት፣ ፍትሐዊነትና እኩልነት ነው። ከዚህ ታሪኩና ሥነ ልቦናው ጋር የሚቃረኑ ተግባሮች በሙሉ ሥርዓት አልበኝነት የወለዳቸው ናቸው።
በሕግና ሥርዓት እንጅ በደቦ ፍርድ የግልም ሆነ የቡድን፤ እንዲሁም የሕዝብም ሆነ የሀገር ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት አይቻልም። ምክንያቱም የስርዓት አልበኝነት የመጨረሻ መዳረሻው ጥፋትና መጠፋፋት ነው።
ስለሆነም የክልላችን ሕዝብ ዘላቂ ሰላሙን ለማረጋገጥ አንዲህ አይነት ሥርዓት አልበኝነትንና ሕገወጥ ተግባሮችን ከመንግሥት ጎን ቆሞ ሊያወግዝና ሊታገል ይገባል።
በወንድማችን አቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን በክልሉ መንግስትና በራሴ ስም እየገለጽኩ፤ ለክልላችን ህዝብ፤ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ በሙሉ መጽናናትን እመኛለሁ።