
የፓርቲያችን ስራ አስፈፃሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልፅግና ፅ/ቤት ሀላፊ የሆኑት በአቶ ግርማ የሺጥላ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ቦታው መንዝ ጓሳ በተባለ አካባቢ ለስራ እየንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት በታጠቁ ፅንፈኞች በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የተሰማንን መሪር እና ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን ለመላ ቤተሰቦቹና ባልደረቦቹ ፈጣሪ ያፅናችሁ ማለት እንወዳለን፡፡
ለመላ የአማራ ህዝብ፣ ለፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ መጽናናትንም እንመኛለን። ፓርቲያችን የአቶ ግርማ የሺጥላን ገዳዮች በአፋጣኝ ተከታትሎ ለህግ እንደሚያቀርብ እና በፍትህ አደባባይም ደሙን በፍትህ እንደሚመልስ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
በሃሳብ የተለየን ሰው በሃሳብ ሞግቶ፤ በአመለካከት የተለየን በአመለካከት ረትቶ መነጋገርና የሚበልጠውን የሚበጀውን ለአገርና ለወገን ፍሬ የሚያፈራውን ሃሳብ ማስፋትና ማጽደል ሲቻል የሰውን ልጅ የመሰለ ክቡር ፍጡር:፣ ያውም እንደ ግርማ የሺጥላ ዓይነቱን የሀገር የህዝብና የወገን አለኝታ የሆነ ምሁር ፖለቲከኛ በእንዲህ ዓይነት መልኩ መግደል መሸነፍ መሆኑን አሁንም ደግመን መናገር እንፈልጋለን፡፡
የአቶ ግርማ በፅንፈኛ ሀይሎች ጥቃት መቀጠፍ ስንሰማ ልባችን በሀዘን ደምቷል። በዚያውም ልክ ፅንፈኝነትን አምርረን መታገልና ማክሰም ግዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነ አሳይቶናል።
በሀገራችን እየታየ ያለው የፅንፈኝነት አስተሳሰብ እና ከአስተሳሰቡ የሚነጩ እኩይ ድርጊቶች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊከቱን እንደሚችሉ ምንም ጥያቄ የለውም። በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ ምልዓተ ህዝቡን ያሳተፈ ጠንካራ የፖለቲካ ትግል በማድረግ እና ህግ የማስከበር እርምጃዎችን በማጠናከር ጽንፈኝነትን ለመግታት ከምንግዜውም በበለጠ ጠንክሮ እንደሚሰራ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።
የብልፅግና ጉዟችን ጽንፈኞች እና ሌቦች እኩይ ተግባር ፈፅሞ አይደናቀፍም!
ወንድማችን ግርማ የሺጥላ ነፍስዎት በአፀደ ገነት ትረፍ!
ብልፅግና ፓርቲ
ሚያዚያ 19/2015