የበርሃ አንበጣን በቀላሉ መከላከል የሚያስችል አሠራር በዚህ ሳምንት ሊሞክሩ እንሆነ አንድ ተመራማሪ ተናገሩ፡፡

453

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 03/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአፍሪካ እና በምዕራብ እስያ ሀገራት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙም ዕውቅና ያልነበረው የበረሃ አንበጣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰብል ላይ ጉዳት በማድረስ ለአካባቢው ስጋት ሆኗል፡፡
በተለይም በሰሜን አፍሪካ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 811 ጀምሮ የአንበጣ መንጋ ምልክቶች ይስተዋሉ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተረጋገጡ መዛግብት እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አልተገኙም፡፡
የበረሃ አንበጣ የሰሜን አፍሪካ በረሃማ ሀገራት፣ የሰሃራ በረሃ የሚያካልላቸው ሀገራት እና በአረብ ምድር በባሕረ ሰላጤው ሀገራት አካባቢ የሚፈለፈል ተባይ ነው፡፡ አንድ የአንበጣ መንጋ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአንበጣ ቁጥር ሊኖረው ይችላል፡፡ ከአንድ ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ አካባቢ ሊሰፍርም ይችላል፡፡ በአንድ ቀን እስከ 100 ኪሎ ሜትር እያሰፋ ሊጓዝም ይችላል፡፡
የዓለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ እንደሚያመላክተው በዓለም ትልቁ የመጨረሻው የአንበጣ መንጋ የተከሰተው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 ባለው ጊዜ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በሰሜን አፍሪካ በ20 ሀገራት ውስጥ ነው፡፡
የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋትም በወቅቱ 13 ሚሊዮን ሊትር ፀረ ተባይ መድኃኒት አስፈልጓል፡፡ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመከላከሉ ወጭ የተደረገ ሲሆን 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት የሰብል ምርትን ደግሞ አውድሟል፡፡ አንድ የአንበጣ መንጋ በቀን 200 ቶን ዕፅዋትን መመገብ ይችላል፤ የዓለምን 20 በመቶ ዛፍን እንዳልነበረ በማድረግ የዓለምን 10 በመቶ ዜጎች የምግብ ጥያቄ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከትትም በ2015 የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጉባኤ ላይ የቀረበ ጥናት ያስረዳል፡፡
ይህ ድርጊት የአከባቢውን ሥነ ምኅዳር ከመጉዳቱ በላይ ለእንስሳት እና ለሰዎች የምግብ ፍጆታ የከፋ የድርቅ ክስተት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡
ያኔም ቢሆን ሀገራት የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ቢያደርጉም፤ 13 ሚሊዮን ሊትር ፀረ ተባይ ቢረጩም፣ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ለሥነ ምኅዳር ጠንቅና ለርሃብ መነሻ ሁኗል፡፡ ሀገራት አንበጣውን የመከላከል ጥረታቸውን ያገዘው ለአንበጣው ምቹ ያልሆነ የአየር ጠባይ በመፈጠሩ እንደሆነም በፋኦ ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

በአማራ ክልል የበረሃ የአንበጣ መንጋ ከተከሰተ ሦስት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ፣ ጊዜ እና ጉልበት መባከኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ሰሞኑን ለምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ 8 ወረዳዎች ላይ አንበጣው መከሰቱን ለምክር ቤቱ ተናግረው ነበር ነገር ግን ከእሳቸው ሪፖርት በኋላ በዋግ ኽምራ ብሔረስብ አስተዳድር እና በሰሜን ሸዋ አንዳንድ ወረዳዎች የበረሃ አንበጣው ተከስቷል፡፡ ይህም የጉዳቱን መጠን እና ወጭ ከፍ ያደርገዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች የተፈጠረውን የበረሃ አንበጣ መንጋን ለመከላከል በዘመናዊው መንገድ በአውሮፕላን ኬሚካል ከመርጨት ባሻገር አርሶ አደሩን ጨምሮ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ዘርፈ ብዙ ባሕላዊ አማራጮች ተወስደዋል፡፡
ይሁን እና የኬሜካል ርጭቱ በተለይ ቆላማ የንብ አካባቢዎች፣ የማር ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ በእንስሳት መኖ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በሀገሪቱ የተቋቋመው የአንበጣ መከላከያ ኮሚሽን ተግባርም በኬሜካል ከመርጨት ውጭ ያቀረበው አማራጭ የመከላከያ ዘዴ የለም፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ሕዝቡ እንደሚያደርገው ሁሉ አንበጣን በከበሮ እና በጥሩንባ፣ በቆርቆሮ እና በጥይት፣ በጩኸት እና ዛፍ በማወዛወዝ ለማስለቀቅ የሚሞክሩ ባለሙያዎች፣ ምሁራን ሲታዩ “ክረምት ሳይኖር ሁሉም ቤት፣ እንግዳ ካልመጣ ሁሉም ሴት” እንደሚባለው ብሂል ሆኗል፡፡

ተቋማት እና ምሁራን በየዘርፋቸው ሊፈጠሩ በሚችሉ አደጋዎች እና ኩነቶች አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ሲያዘጋጁ እና ሲያመላክቱ አይስተዋሉም፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመሥገን ለምክር ቤት አባላት በአንበጣው ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ እንዳልተቻለ እና መፍትሔውም በቀጣይ ሳምንት በሚኖረው የአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት እንደሚጠፋ ተስፋ እንደሚያደርጉ መናገራቸው የዚህ ውጤት ነው፡፡ ይህም አማራጭ መፍትሔም ሆነ ጉዳትን ማወቅ የሚያስችል አሠራር አለመኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አዲስ መኮንን (ዶክተር) ግን “አንበጣው ከተፈጠረ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንቅልፍ በማጣቴ ለሦስት ቀናት አጥንቼ ጊዚያዊ አማራጭ መፍትሔ ይፋ አድርጌያለሁ፤ በኬሜካል መርጨት የጎንዮሽ ጉዳት አለው፤ ማባረርም መፍትሔ አይደለም” ብለዋል፡፡ ዶክተር አዲስ አንበጣው እንቁላሉን ሳይጥል ይዞ መግደል የሚያስችል ከመረብ የተሠራ አዲስ የመፍትሔ አማራጭ ማቅረባቸውንም ምሁሩ አስረድተዋል፡፡

ዶክተር አዲስ የሠሩት የአንበጣ ምግብ የሚመስል አረንጓዴ ቀለም ያለው መረቡ በአንድ ጊዜ እስከ 40 ሺህ አንበጣ መያዝ የሚችል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር አዲስ መረቦችን በብዛት ሰርቶ ማሰራጨት እንደሚቻል አመላክተው 10 ሺህ መረቦች በአንድ ቀን እስከ 400 ሚሊዮን አንበጣ መያዝ የሚያስችላቸው በመሆኑ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለሙከራ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡

‹‹አንበጣ ለሥነ ምግብ ከፍተኛ ንጥረ ነገር ያለው በመሆኑ በውጭ ሀገራት በከፍተኛ ዋጋ ለምግብነት ከሚቀርቡት ውስጥ አንዱ ነው›› ያሉት ዶክተር አዲስ በኢትዮጵያ ግን በመረቡ የተያዘውን አንበጣ ለእንስሳት መኖ ማዋል የሚቻልበት ዕድልም እንዳለ አመላክተዋል፡፡

አንበጣን ለመከላከል አሁን በሀገሪቱ እየተተገበረ ካለው ባሕላዊ የማባረር ዘዴም ሆነ በኬሜካል ከሚረጨው ዘዴ በተሻለ መንገድ የተለያዩ የብርሃን ቀለማትን በመጠቀም እና “በቫኪዩም ፓንፕ” አንበጣውን በመሳብ ወደ መረቡ ማስገባት የሚቻልባቸውን የተሻሉ አማራጮች በመጠቀም ለማጎልበትም ሊሠሩት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

“ተቋማት በሀገሪቱ መሰል ድንገተኛ ችግሮች ሲያጋጥሙ በባሕላዊ አካሄድ የዜጎችን ጉልበት በመጠቀም በዘልማዳዊ አሠራር ነው ለመፍታት የሚሞክሩት” ያሉት መምህሩ፣ ሳይንሳዊ የመከላከያ እና የመጠባበቂያ ዘዴዎች ሊኖሯቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ለድንገተኛ ክስተቶችም ሆነ ለዘላቂ መፍትሔዎች ችግርን ወደ ዕድል ለመለወጥ የሚያስችሉ አማራጮችን ዝግጁ በማድረግ ተቋማት እና ባለሙያዎች የዘወትር ተግባራቸው ሊያደርጉ እንደሚገባም ምሁሩ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleፕሮጀክቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ትልቅ ሚና አለው ተባለ፡፡
Next articleበዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ21 ሺህ በላይ ተማሪዎች አልተመዘገቡም ተባለ፡፡