
በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በተከበሩ አቶ ግርማ የሺጥላ፣ በግል ጥበቃዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በአካባቢው ላይ ሠርተው ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን እየመጡ በነበረበት ሰዓት መንዝ ጓሳ ላይ በታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሟል፡፡
በዚህም አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ እስካሁን በደረሰን መረጃ የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በደረሰው ልብ ሰባሪ ጥቃት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰማውን መሪር ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል፡፡
እንዲህ አይነት አጥፊዎች እያደረሱት ያለው መረን የለቀቀ የሽብር ድርጊት ክልሉን እየመራ ያለውን መንግሥትና መላውን ሕዝብ የበለጠ ሊያጠናክር እንጂ በጥፋት ሃይሎች ሴራና ፍላጎት የሚሳካ ምንም አይነት ተልዕኮ የለም፡፡
ስለሆነም ይህንን የሽብር ሥራ እየሠሩ ያሉ እንዲህ አይነት ኃይሎች ላይ የክልሉ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል፡፡ የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ ያቀርባል፡፡ ማንኛውም በእንደዚህ አይነት ድርጊት የተሳተፉ ኀይሎችንንና ተባባሪዎችን ሁሉ ከያሉበት ለሕግ በማቅረብ አስፈላጊው ፍትሕ እዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡
በመሆኑም መላው የክልላችን ሕዝብ የተፈጠረውን የሽብር ድርጊት ከማውገዝ ጀምሮ ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ፍትሕ እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና እንዲረጋጋ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የጥፋት ኃይሎች ከዚህ በላይ ዓላማ ያላቸው እና ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት እንደማይታገስ እና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ እናረጋግጣለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር