“በዩኒቨርሲቲዎች በኦንላይን ለሚካሄደው የመውጫ ፈተና 30 ሺህ ኮምፒውተሮች ዝግጁ ሆነዋል” የትምህርት ሚንስቴር

127

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመጪው ሀምሌ ወር በዩኒቨርሲቲዎች በኦንላይን ለሚካሄደው የመውጫ ፈተና 30 ሺህ ኮምፒውተሮች ዝግጁ መሆናቸውን የትምህርት ሚንስቴር ገለጸ።
በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሰይድ መሀመድ ለኢቢሲ እንደገለጹት፤ ከ240 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና የማያልፉ ተማሪዎች ዲግሪ የማይሰጣቸው በመሆኑ ተማሪዎች ለሚሰጠው ፈተና ራሳቸውን አንዲያዘጋጁ ኃላፊው አሳስበዋል።
በሀምሌ ወር ከሚሰጠው ፈተና በፊት በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የሙከራ ፈተና እንደሚሰጥም ነው የተገለጸው።
በኦንላይን ፈተናው መሰጠቱ ኩረጃን ለማስቀረት፣ የወረቀት ወጪና ማጓጓዣን ለመቀነስ ይረዳል ብለዋል ኃላፊው።
ለፈተናው በአጠቃላይ ከ15 በላይ ኮርሶች በየትምህርት መስኩ ተወጣጥተው ዝግጁ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሰይድ ፤ የፈተናው ውጤት በኦንላይን ይፋ የሚደረግና ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ፈተናውን የማያልፉ ተማሪዎች ያለገደብ በተደጋጋሚ የመፈተን ዕድል እንደሚኖራቸው በመመሪያ መቀመጡን ነው ኃላፊው የገለጹት።
የመውጫ ፈተናው የተለየ ዓላማ የሌለው እና የተማሩትን ብቻ የሚመዝን በመሆኑ ሳይደናገጡ እንዲዘጋጁ ለተማሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመፈተኛ ጣቢያ እንደሚሆኑም ኃላፊው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
Next articleከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ