
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች የ5 ሚሊየን ብር የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ድጋፉን ሲረከቡ እንደተናገሩት በከተማው በግለሰብ ቤት ተጠግተው የሚኖሩት ሳይጨምር በመጠለያ ካምፕ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ጠቅሰው የምግብ፣ የመጠለያና የአልባሳት ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ህፃናት፣ አቅመ ደካሞችና ሴቶች በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የወገኖቻችን ችግር የእኛም ችግር ነው ብሎና በጎ አድራጊ አካላትን አስተባብሮ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል፡፡
በረመዷን ወቅትም ሆነ በኢድ አልፈጥር በዓል በመጠለያ የሚገኙ ሙስሊም ወገኖቻችን ሳይከፋቸው እንዲያከብሩ በዚህ ዓመት ከወትሮው በተለየ መልኩ የታየው መተባበር መልካም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
2 ሄክታር በማይሞላ ቦታ ውስጥ እስከ 12 ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ተጨናንቀው ለመኖር መገደዳቸውን ከንቲባ በድሉ አስረድተዋል፡፡ሁኔታዎች ተስተካክለው በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ሌሎች አካላትም ሆኑ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ፈቱዲን ሀጂ ዘይኑ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ተባብረው ድጋፉን አሰባስበው ይዘው በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከላይ እስከታች ያለው የእስልምና ምክር ቤት ተቀናጅቶ በተለያዩ የሀገር የልማትና የበጎ አድራጎት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡የሕዝባችን ችግር የእኛም ችግር ስለሆነ ዛሬም ነገም ከጎናችሁ ነን ብለዋል፡፡
እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከችግራቸው እስኪወጡ ድረስ የሃይማኖት ተቋማት፣ባለሀብቶች፣የሚመለከታቸው አካላትና ሁሉም ሰው ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡በዚህ ሥራ የተሳተፉ የአዲስ አበባ እና በሀገሪቱ የሚገኙ የሙስሊም ማኅበረሰብ እንዲሁም ያስተባበሩ አካላትን አመስግነዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሊድ መሀመድ እንደተናገሩት የዛሬው ድጋፍ ሃይማኖትን ወይም ብሄርን መሠረት ያደረገ ሳይሆን የዜጎች ጉዳት የእኛ ጉዳት ስለሆነ ድጋፉን ከአዲስ አበባና ከውጪ ጭምር አሰባስበናል ብለዋል፡፡ተቋማቸው ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ስራዎችንም እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ይዘውት የመጡት ድጋፍ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ ዱቄት፣ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት መሆኑን ጠቅሰው ከቁጥራቸው ጋር ሲነፃጸር በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አሳዛኝ ነው ያሉት አቶ ካሊድ ችግሩን ለመቀነስ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ወደፊትም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን የደብረብርሃን ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!