“የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በማጠናከር የተሻለች ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ” አቶ አደም ፋራህ

61

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥትና ብልፅግና ፓርቲ በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በማጠናከር የተሻለች ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ለልኡክ ቡድኑ በመቀሌ ለተደረገው ኢትዮጵያዊ ስሜት የታየበት ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለረጅም ዘመናት መታገሉን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን መፃዒ ዕድላቸው እጅግ የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት በተሟላ መልኩ የሚሳካው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ወንድማማችነቱን አጥብቆ በጋራ መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።
መንግሥትም የብልፅግና ፓርቲም የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ሕዝብ በፍጥነት መልሶ እንዲቋቋም በቁርጠኝነት ይሠራሉ ነው ያሉት።
በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም በመተባበር በፍጥነት ማገገም እንደሚቻል ተናግረዋል።
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከንቲባዎች ጉብኝት ሰላምን የማፅናት አብሮነትን በተግባር የመግለጥ ጉዞ ነው ብለዋል።
የልዑካኑ ጉብኝት የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጎዱ አካባቢዎችን በጋራ ለመገንባት ያለውን ዝግጁነት የሚገልጽ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ በማጠናከር ሁሉንም አቅሞች አጠናክሮ ሕዝቡን ከደረሰበት ጉዳት ለማውጣት በትጋት መሥራቱን ይቀጥላል
ለዚህም በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያንና አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀሙሲት ከተማ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሊገነባ ነው፡፡
Next articleየአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።