
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀሙሲት ከተማ በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጭ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ለመገንባት የውኃና ኤነርጂ ሚኒስቴርና የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የውል ስምምነትም ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ ላይ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል ብለዋል።
አካባቢው በውኃ አቅርቦት ችግር ውስጥ ያለ በመኾኑ በተደረገው ስምምነት ደስተኞች ነን ነው ያሉት፡ ሚኒስትሩ በሂደቱ ለነበሩ ተግባራትና አጋዥነታቸውን ላሳዩ የክልል የሥራ ኀላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በበኩላቸው፤ የተለያዩ ጥረቶች ቢኖሩም መጓተቶች ተስተውለውበት የነበረ የውኃ ፕሮጀክት በመኾኑ አሁን በተደረሰው ስምምነት ፈጥኖ ግንባታው እንዲጠናቀቅ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡
ይህ የውል ስምምነት የተደረገውና ግንባታው የሚከናወነውም ከዓለም ባንክ፣ ከፌዴራል መንግሥትና ከክልል በተገኘ በጀት መኾኑም ተገልጿል፡፡ ግንባታው በአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እንደሚከናወን ነው የተብራራው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም በሀሙሲት ከተማና አካባቢው ላሉ 84ሺህ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል።
የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዘመነ ፀሐይ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በተሰጣቸው ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፦ እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!