
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የየብስ ትራንፖርት መጀመሩን አስመልክቶ የአማራ ክልል፣ የአፋር ክልል እና የፌዴራል የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ ስጥተዋል።
በአማራ ክልል አቅጣጫ ዛሬ 4ኛ ቀኑን የያዘ የሕዝብ ትራንስፓርት የሙከራ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ መደረጉን የገለጹት የአማራ ክልል የትራንፖርት እና የሎጀስቲክስ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወርቁ ያየህ ናቸው። 3 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች በአማራ ክልል በኩል ጉዞ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ይፋዊ ጉዞ መጀመሩን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ለማንኛውም የትራንፓርት እና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። የክልልሉ ሕዝብም ለሰላማዊ እንቅስቃሴ በጎ አመለካከት ያለው በመኾኑ ጉዞው ላይ ችግር እንደማያጋጥምም አረጋግጠዋል።
በአፋር ክልል በኩል በመጀመሪያው ቀን ብቻ ሁለት የሙከራ ጉዞዎች መደረጋቸውን እና ትራንስፖርት ከተጀመረ ደግሞ 6 ቀናት ማስቆጠሩን የአፋር ክልል የትራንፖርት እና መንገድ ቢሮ ምክትል ኀላፊ መዲና መሐሙድ ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሰላማዊ እንዲኾን ያግዛልም ነው ያሉት፡፡ ቢሮ ኀላፊዋ መንግሥት ብቻ ሳይኾን ሕዝቡም ሰላማዊ አንቅስቃሴውን እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል። ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ይፋዊ የየብስ ትራንፖርት ጀምሯል ብለዋል።
የትራንፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ድኤታው በርኦ ሀሰን እንዳሉት በሰሜኑ ጦርነት ተፈጥሮ በነበረው አላስፈላጊ ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የየብስ ትራንፖርትን ለማስጀመር ሁለት የጥናት ቡድን በአማራ ክልል በኩል እና በአፋር ክልል በኩል በመላክ ጥናት መደረጉን አንስተዋል፡፡ በዚህ መሰረት በሁለቱም ክልሎች በኩል 19 የሙከራ ጉዞዎች ከአዲሰ አበባ ትግራይ ክልል እና ከትግራይ ክልል አዲስ አበባ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ይፋዊ የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩን አረጋግጠዋል።
የትግራይ ክልል የትራንፖርት ቢሮ ኀላፊዎች በአየር ትራንፖርት መዘግየት ምክንያት በአዲስ አበባ በተሰጠው የጋራ መግለጫ ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው ተነግሯል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!