
👉የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም ከሚያዚያ 21 -22 /2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል ።
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ከአዲስአበባ ከተማ አሥተዳደር ጋር በትብብር በሚያዘጋጁት የከንቲባዎች ፎረም ከ300 በላይ የከተማ ከንቲባዎች ተሳታፊ እንደሚኾኑ የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገልጸዋል። ሚንስትሯ በሰጡበት መግለጫ የሁሉም ክልል ርዕሳነ መሥተዳደሮች በፕሮግራሙ እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። እንግዶች ከሚያዝያ 20 ጀምሮ ወደ መዲናዋ እንደሚገቡም ተናግረዋል ።
የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት በቀጥታ ከከተሞች ልማትና ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የተናገሩት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደ ሀገር ከተሜነት ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ቢኾንም ዕድገቱ የዕድሜውን ያህል እዳልኾነ ተናግርዋል።ፕሮግራሙ በከተሞች ልማትና ዕድገት ላይ ጥሩ መነቃቃት እንደሚፈጥርም ይጠበቃል።
በከተሞች መካካል ያለውን እህትማማችነት ማጠናከርም የፎረሙ ሌላኛው ዓላማ ነው። በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት በአማራ፣በአፋር ፣ በትግራይ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር ውድመትና መጎሳቆል የደረሰባቸውን ከተሞች መልሶ ለመገንባት ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ከተሞችን ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር በማስተሳሰር የከተሞችን ዕድገትና ከተሜነት ለማዘመን ይሰራልም ተብሏል ።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!