
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ምርምር ማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዳነ ባሕሩ (ዶ.ር) ሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል በጦርነቱ ከዋናው የምርምር ማዕከል እስከ ምርምር ጣብያዎች ድረስ ግኝቶች እና ቁሳቁሶች በከፍተኛ ሁኔታ ቢወድሙበትም ከደረሰበት ጉዳት በፍጥነት ለማገገም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ማዕከሉ ለማገገምም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እስከ ዘንድሮ የሰብል ልማት እንቅስቃሴ በ500 ሄክታር መሬት ላይ ከ1 ሺህ 150 በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማባዛት እና በቴክኖሎጂ የማዳረስ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አዳነ አርሶአደሮቹ በጦርነቱ ምክንያት የዘር እጥረት እና የዘር መጥፋት አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል ። የምርምር ማዕከሉ በአስቸኳይ አዳዲስ ዝርያዎች በምርምር የማፍለቁን ሥራ ለጊዜው በማቆም ለመጪው ክረምት ለአርሶአደሮች ተደራሽ ለማድረግ ነባር ዝርያዎችን የማባዛት ሥራ በከፍተኛ ርብርብ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው በመጪው ክረምት በከፊል ሰሜን ወሎ እና በቅርቡ ነጻ የወጡትን ጨምሮ በሁሉም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወረዳዎች 20 የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ ለማድረስ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ዝርያዎች በአማካኝ ከአንድ ሄክታር 13 ነጥብ 5 ኩንታል የሚያስገኙ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከሉ ከሰብል ልማት ባሻገር የአፈር፣ የውኃ ልማት እና የደን ልማት እያከናወነ ነው። የእንስሳት ልማትና ጥበቃ ዘርፎችንም ለማዘመን እና ለማሻሻል እየሠራ ነው ያሉት ዶክተር አዳነ በሰብል ዝርያዎች ከዚህ በፊት 18 ዝርያዎችን ማላመድና ማባዛት ችሏል። ‹ሰቆጣ አንድ› የሚባል ስንዴ እና ‹የዋግነሽ› የሚባል የአተር ምርጥ ዝርያን በማፍለቅ ውጤታማ ሥራ አከናውኗል ብለዋል፡፡
ዶክተር አዳነ ማዕከሉ የሚያሰራጫቸውን የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን አርሶአደሩ ምርጡን ዘር ከመጠቀም ባሻገር የተሞላ ፓኬጅ እየተጠቀመ ባለሙኾኑ የበለጠ ምርታማ መኾን አልተቻለም ነው ያሉት፡፡ ይህንን ውስንነት በመቅረፍ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና የግብርና ባለሙያዎች ከፍተኛ እገዛና ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
ዚጋቢ ፡- ግርማ ተጫነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!