ፕሮጀክቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ትልቅ ሚና አለው ተባለ፡፡

201

የአማራ ክልል ‹የገጠር ልማት ስትራቴጂና ሞዴል መንደር ማማከር ፕሮጀክት› ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ መሠረት እንደሚጠል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልል የገጠር ልማት ስትራቴጂና ሞዴል መንደር ማማከር ፕሮጀክት ከክልሉ አመራር አካዳሚ ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሮች እና ለአመራሮች ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል፡፡ የስልጠናው ዓላማ በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ሀብት ልማት አና አካባቢን በማሻሻል ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት የኮሪያን ልምድ ማስገንዘብ ነው፡፡ ኮሪያ ከአስከፊ ድህነት በመላቀቅ ለደረሰችበት ደረጃ የተጠቀመችበትን የአዲስ መንደር ንቅናቄ ምሥረታ ተግባራዊ በማድረግ በክልሉ ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲኖር ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡
የኮሪያን የገጠር ልማት መሠረት አድርጎ የተጀመረው ፕሮጀክቱ በአራት ዞኖች በሚገኙ አራት ወረዳዎች እና 20 መንደሮች ውስጥ ያሉ ከ 3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተግባራዊ እያደረጉት መሆኑንም ነው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መልኬ ታደሰ የተናገሩት፡፡
በደራ ወረዳ 22 አርሶ አደሮች የ‹ግሪን ሀውስ› ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ በትንሽ ቦታ የተሻለ ምርት እና ገቢ ማግኘት የቻሉበት የአሠራር ዘዴ ተግባራዊ መደረጉንም ነግረውናል፡፡ ፕሮጀክቱ በተጀመረባቸው አካባቢዎች የተሻለ ውጤት መገኘቱን ያመላከቱት አስተባባሪው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በማስፋፋት የክልሉን ሁለንተናዊ ለውጥ የማምጣት ዓላማን እውን ለማድረግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ መሠረት ይጥላል፡፡

ከጥቅምት 28/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለመንደር መሪ አርሶ አደሮች እና በየደረጃው ለሚገኙ መሪዎችች ሲሰጥ የነበረው ስልጠናም የአርሶ አደሮችን አቅም በመገንባት እንዲሁም የባለሙያዎችን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ዕውን ለማድረግ የጎላ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ መሰል ስልጠናዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ በአመራር አካዳሚ አማካኝነት እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ መልኬ በወረታ እና በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጆች እስከ 700 የሚደርሱ መሪዎችን ለማሰልጠን እቅድ ተይዟል፡፡

ያነጋገርናቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ካደረጉ በኋላ የግብርና ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነግረውናል፡፡ በቀጣይም በስፋት ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው አስተያዬት ሰጭዎቹ የተናገሩት፡፡ ከዚህ ባለፈም የግጭት ምንነት፣ መንስዔዎች እና የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በስልጠናቸው መመልከታቸውን አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል ያለው የመልማት ፀጋ ምን እንደሚመስል እና በምን መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ነው ሰልጣኞቹ የተናገሩት፡፡ ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን ልምድ ለአካባቢያቸው ማኅበረሰብ እንደሚያካፍሉም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበሴካፋ ውድደር የሚጫወቱት ሉሲዎቹ ወደታንዛኒያ አቅንተዋል፡፡
Next articleየበርሃ አንበጣን በቀላሉ መከላከል የሚያስችል አሠራር በዚህ ሳምንት ሊሞክሩ እንሆነ አንድ ተመራማሪ ተናገሩ፡፡