በጎንደር በረሀማ አካባቢዎች የሚገኙት የ “በጋይት” ዝርያ ያላቸው ላሞች፣ ከፍተኛ የወተት ምርት እየሰጡ ነው፡፡

99

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእድገታቸው እና በእርባታ ሂደታቸው ፈጣን የኾኑት የበጋይት ዝርያ ያላቸው የቀንድ ከብቶች፣ በጎች እና ፍየሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡
ዝርያቸው ከሱዳን እና ኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች እንደሚነሳ በባለሙያዎቹ ዘንድ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ክልል በተለይም በጎንደር በረሀማ አካባቢዎች በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በርካታ አካባቢዎች እና በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ አካባቢ ብቻ ይገኛል፡፡ የበጋይት ዝርያ የቀንድ ከብት፣ በግ እና ፍየልን ያጠቃልላል፡፡ ከተለመደው ውጭ ፈጣን የርቢ ሥርዓት፣ ተመራጭ ሥጋ እና የሥጋ ውጤት እንዳላቸውም ይነገራል፡፡

ባለሀብቱ አቶ አስማረ መስፍን በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የቃብቲያ ሁመራ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከተሰማሩበት ዘርፈ ብዙ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል የበጋይት ዝርያ ያላቸው እንስሳት እርባታ አንዱ ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ብቻ ከ200 ያላነሱ የቀንድ ከብቶችን የሚያረቡት ባለሀብቱ “በርሃማው የአየር ንብረት የሚስማማቸው በጋይቶች ፈጣን የርቢ ሥርዓት፣ ተመራጭ ሥጋ እና የሥጋ ውጤት አላቸው” ይሉናል፡፡ የበጋይት ዝርያ እድገታቸው እና የእርባታ ሂደታቸው ፈጣን ከመኾኑ ባሻገር የወተት ምርታቸውም ከፍተኛ መጠን ያለው ነው፡፡ በአሁናዊው ገበያ አንድ የበጋይት ዝርያ ያለው በሬ እስከ 80 ሺህ ብር ይሸጣል የሚሉት አቶ አስማረ ላሞቹ እስከ 60 ሺህ ብር ድረስ ዋጋ ያወጣሉ ብለውናል፡፡

በዓመት ከ50 እስከ 60 የቀንድ ከብቶችን ለገበያ እንደሚያቀርቡ ያጫወቱን ባለሀብቱ ከሦስት ሚሊየን ብር ገቢ ይገኛል ነው ያሉን፡፡ የበጋይት ዝርያ በዞኑ ውስጥ በስፋት ይታወቃሉ ያሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኅላፊ አቶ አወቀ መብራቱ ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት እና ተከስቶ በነበረው ጦርነት ዝርያቸው ተመናምኖ ነበር ብለውናል፡፡

በአካባቢው ተፈጥሮ ከነበረው ጦርነት በፊት የበጋይት ዝርያ ያላቸው 400 ሺህ በላይ የሚኾኑ የበጋይት ዝርያ ነበሩ ያሉት ኅላፊው በጦርነቱ ወቅት እስከ 250 ሺህ ድረስ ወርዶ ነበር ብለውናል፡፡ የበጋይት ዝርያ ከአማራ ክልል ውጭ በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢ የተለመደ አይደለም ያሉት ኅላፊው፤ ለበጋይቶች በርሃማ አካባቢ ምቹ እንደኾነ ይታመናል ነው ያሉት፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የተመናመነውን የበጋይት ዝርያ ለመመለስ ብዙ የግብርና ኤክስቴንሽን አይጠይቅም የሚሉት ኅላፊው አርሶ አደሩም ኾነ ባለሀብቱ ጥቅማቸውን ስለሚያውቅ በትንሽ ጥረት ብቻ ወደነበረበት መመለስ ይቻላል ብለዋል፡፡
በሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማዕል ውስጥ ከ2 ሺህ በላይ የቀንድ ከብት፣ በግና ፍየል የበጋይት ዝርያ ነበር ያሉት አቶ አወቀ በጦርነቱ ወቅት ዘረፋ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የምርምር ማዕከሉ ከፍተኛ ውድመት እና ዘረፋ ስለተፈጸመበት ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የምርምር ማዕከሉን ወደ ሥራ ለማስገባት የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስፖርት ዜና ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ)
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ።