ያለልማት ለዓመታት የቆመው የኢንዱስትሪ መንደር!

120

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ገበያ ተኮር ምርቶች ከሚመረቱባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፤ በእንስሳት ሃብትም ከፍተኛ አቅም ያለው ቀጣና ነው ምዕራብ ጎንደር ዞን።
ዞኑ ለግብርና ካለው አቅም አኳያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከ1 ቢሊዮን 106 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 28 ፕሮጀክቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቻ ፈቃድ ቢወስዱም በተቀመጠላቸው ውል መሠረት ወደ ሥራ መግባት አልቻሉም። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ደግሞ በገንዳ ውሃ ከተማ የሚገኘው “ካልሚ” የዘይት ፋብሪካ አንዱ ነው።

ፋብሪካው በ2009 ዓ.ም ወደ ግንባታ እንደገባ የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ማስረሻ ኃይሌ ነግረውናል። በ2013 ዓ.ም ደግሞ የዘይት ድፍድፍ ማምረት ጀምሮ ከሌላ አካባቢ ይመጣ የነበረውን የከብቶች መኖ ጭምር ማስቀረት ችሎ ነበር። ይሁን እንጅ ለማምረት የተዘጋጀው ፋብሪካ በብድር አቅርቦት ችግር ምክንያት ሥራ አቁሟል። ለባንኮችና ዋሊያ ካፒታል ብድር ጠይቀው እንዳልተሳካም ነው ሥራ አስኪያጁ የገለጹት።

ፋብሪካው በአካባቢው የሚመረተውን የጥጥ ፍሬና ሰሊጥ ምርት በግብዓትነት ይጠቀማል። ምርቱንም ወደ ውጭ ለመላክ ጭምር እቅድ ነበረው። የብድር አቅርቦት ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዳይገቡ ማነቆ ቢኾንም መሬት ወስደው የብድር ማግኛ መጋዝን ከገነቡ ኋላ ለረጅም ጊዜ የሚጠፉ ባለሃብቶች መኖራቸውንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። አበዳሪ ተቋማት የፕሮጀክቶችን ትክክለኛ የሥራ የሰነድ የመመርመር ችግር መኖሩንም ነው ያነሱት።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ እና የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ቡድን መሪ ዳንኤል ዓለሙ እንዳሉት በገንዳውሃ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ግንባታ አጠናቅቀው ወደ ሥራ ያልገቡ እና ባቀረቡት ሃሳብ መሠረት ወደ ሥራ ያልገቡ 28 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ግንባታ አጠናቅቀው በተቀመጠላቸው ጊዜ ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን ለመንጠቅ የሚያስችል መመሪያ ወደ ዞኑ ባለመውረዱ ዞኑ የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ ከመስጠት ያለፈ ሥራ አለመሥራቱን ገልጸዋል። ክልሉም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ፕሮጀክቶች በውላቸው መሠረት በተቀመጠው ጊዜ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው በአካባቢው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ይኸነው ዓለም እንዳሉት በኢንቨስትመንት ስም ሸዶችን በመገንባት ብድር ወስዶ መጥፋትና ብድር ለመበደር የሚያስፈልገውን መስፈርት አሟልቶ ባለመቅረብ ምክንያት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ወደ ሥራ እንዳይገቡ አድርጓቸዋል።

ባንኮችም ከዚህ በፊት ያበደሩት ብድር ካልተመለሰ ተጨማሪ ብድር እንደማይሰጡም ኀላፊው ገልጸዋል። በብድር አቅርቦት ችግር ሥራ እንዳቆመ ያነሳው ካልሚ የዘይት ፋብሪካም ከዚህ በፊት የወሰደውን ብድር ባለመመለሱ ተጨማሪ ብድር አለማግኘቱን ነው የገለጹት።

በተቀመጠው ውል መሠረት ወደ ሥራ ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይም መጋዝን ገንብተው የጠፉም ኾኑ በተለያየ ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ ፕሮጀክቶች የወሰዱትን መሬት በመንጠቅ ማልማት ለሚችሉ ባለሃብቶች የማስተላለፍ ሥራ እንደሚሠራ አንስተዋል።

አጠቃላይ የኢንዱስትሪ መንደሩ 181 ሄክታር መሬት ላይ ነው ያረፈው።
👉 ፕሮጀክቶቹ ከ1 ቢሊዮን 106 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።
👉 ከ2 ሺህ 600 በላይ ዜጎች በቋሚና በጊዚያዊ የሥራ እድል የመፍጠር አቅምም አላቸው።
👉 የግንባታ ዘመናቸውም ከ2002 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ነው።
👉በዞኑ በዚህ በጀት ዓመት 162 የሚሆኑ ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል።
👉ባለሃብቶቹ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።
👉400 ሄክታር የኢንድስትሪ ቦታ ተለይቷል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ129 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ” የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ።