“ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ129 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ” የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች ጽሕፈት ቤት

60

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣናው በተደጋጋሚ በሚከሰተው የሰላም መደፍረስ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ቢኾንም ፈተናውን በመቋቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዓመታዊ እቅዱን 83 ነጥብ 5 በመቶ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል::

የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ኑሩ ሁሴን ኢብራሂም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአካባቢው ብሎም በሀገር ደረጃ በነበሩ የሰላም እጦቶች የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ በጸረ ሰላም ኃይሎች በተፈጸሙ ዝርፊያዎችና የንብረት ውድመቶች የንግዱ ማኀበረሰብ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል::

ይሁን እንጅ ከንግዱ ማኀበረሰብ ፣ ከባለድርሻና አጋር አካላትጋር በመወያየት የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያነቃቁ ባዛሮችን በማድረግ ብሎም የሶስት ወር የግብር ቅናሽ በማድረግ ነጋዴው ከተስፋ መቁረጥ ወጥቶ ወደ ሥራው እንዲገባ ማድረግ ተችሏል ብለዋል ኀላፊው::

በዚህም ካለፉት ሁለት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ የገቢ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል::
ለአብነት የ2014 የዘጠኝ ወራት የመደበኛ እና የከተማ አገልግሎት ገቢን አፈጻጸም ለማሳያነት ያነሱት ኀላፊው አምና በዚህ ወቅት መሰብሰብ የተቻለው የእቅዱን 50 ነጥብ 41 በመቶ ብቻ እንደነበረ ተናግረዋል::

በዘንድሮው የበጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዓመቱ ከተያዘው አጠቃላይ 155 ሚሊዮን 425 ሺህ 294 ብር የገቢ እቅድ ከ129 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ማሳካት ተችሏል::
አቶ ኑሩ ሁሴን ሸማቹ ኀብረተሰብ ደረሰኝ የመጠየቅ ልምዱን በማሻሻል ደረሰኝ የማይሰጡ የንግድ ተቋማትን በማጋለጥ ለገቢ አፈጻጸሙ መሳካት የሚጠበቅበትን ሚና በቀጣይ እንዲወጣም አሳስበዋል::

ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዕድገታችን የሚለካው ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ በምናደርገው መዋቅራዊ ለውጥ ነው” ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ
Next articleያለልማት ለዓመታት የቆመው የኢንዱስትሪ መንደር!