
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ኢንደስትሪ ሚኒስቴር፣ የክልልና የከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ እና የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በምክክሩ ትኩረት ተሰጥቶት ይገመገማል ተብሎ ይጠበቃል። በምስራቋ የኢትዮጵያ ፈርጥ ሱማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ በተጀመረው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ “ዕድገታችን የሚለካው ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ በምናደርገው መዋቅራዊ ለውጥ ነው” ብለዋል።
ኢንደስትሪ ዘርፉ ለኢኮኖሚያችን ማደግ ትልቅ ሚና ያለው ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሱማሌ ክልል በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ያላገኘ ዘርፍ መኾኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ ለዚህም የፀጥታ ችግር ፣ የአቅም ውስንነትና ኢንቨስተሮችን ለመሣብ ምቹ ሁኔታዎች በተፈለገው መጠን አለመሟላት ስለመኾናቸው በምክንያትነት አንስተዋል። ነገር ግን አሁን በተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና ክልሉ ውስጥ በተፈጠረው የተሻለ ሠላም ዘርፉ እንዲነቃቃ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ ለብዙ ወደቦች ቅርብ መሆኑ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማሻገር ምቹ ሁኔታ አለ ነው ያሉት። ምክክሩ በጂግጂጋ መደረጉ ለክልሉ ትልቅ ግብዓት እንደሚኾንም ነው ያነሱት፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ በክልሉ በሚኖረው ምክክርና የመሥክ ምልከታ ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን በመለየት ድጋፍ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ክልሉ ያሉትን በርካታ ሃብቶች እንዴት እየተጠቀማቸው ነው? እንዴትስ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ማድረግ ይቻላል የሚለውን የክልሉን ተሞክሮ ለማየትም ያስችላል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። በተለይም በሱማሌ ክልል ያለውን የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተሞክሮ ፈትሾ ወደ መሀል ሀገር ወስዶ መጠቀም እንደሚገባም አስረድተዋል።
እስካሁን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም አንስተዋል።
እንጀራን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ 28 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የሰላም ጉዳይ የአመራሩ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ሕዝቡም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት ኢንዱስትሪ ሰላም እንደሚፈልግ ያነሱት ሚኒስትር መላኩ በዚህም በኢንዱስትሪ ማደግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ንቅናቄውም ከዘመቻ ያለፈ የ10 ዓመት ጉዞ ያለው በመኾኑ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!