“ኢትዮጵያን አሁን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር አድርገናታል” የገንዘብ ሚኒስቴር

54

አዲስ አበባ: ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት አድርጉ የተሰኘ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ መካሔድ ጀምሯል። በዚህ የኢንቨስትመንት ፎረም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ኢንቨስተሮች፣ ኢትዮጵያውያን አልሚዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ሁሉም የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች ተገኝተዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለመኾን ብዙ በሮቿን እየከፈተች ትገኛለች ብለዋል። ኮሚሽነሯ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የሎጀስቲክ፣ የባንክና የቱሪዝም ዘርፎችን ክፍት አድርጋለች ነው ያሉት።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከአካባቢው ጋር የተስማሙ እና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዳቸውን ያሟሉ በርካታ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብታለች፤ ወደፊትም ታስፋፋለች ብለዋል። አንደኮሚሽነሯ ገለጻ ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለአልሚዎች ምቹ ነው። “በማንኛውም ሁኔታ አገልግሎታችንን አሻሽለን እና ክፍት አድርገን የተሻለ አገልግሎት እንደምንሰጣችሁ እንደመንግሥት ቃል እንገባለን” ነው ያሉት።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሸዴ በበኩላቸው “ይህንን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፎረም ስናዘጋጅ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ከውስጥ ቀርፈን ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አምስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገራት አንዷ ኾናለች ያሉት ሚኒስትሩ ከአፍሪካ በፈረንጆቹ 2021 ብቻ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች ነው ያሉት። በ2023 ደግሞ 4 ነጥብ 26 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የማምጣት እቅዷን በመተግበር ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የንግድ ሕጓን አሻሽላለች፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አሠራር መመሪያዎችን ወደ ሥራ አስገብታለች፤ የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራሮችን እየተከተለች ነው። በእነዚህ እና በሌሎች አማራጮች “ኢትዮጵያን አሁን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሀገር አድርገናታል” ብለዋል።

በዚህ የኢንቨስትመንት ፎረም በኢትዮጵያ ውስጥ ለኢንቨስትመንት አስቸጋሪ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ለወደፊት ይጠቅማሉ የተባሉ ሃሳቦችም ተነስተው ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ ይደረጋል ነው የተባለው።
ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት አድርጉ በሚል የተዘጋጀውን ፎረም የኢፌዴሪ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ናቸው ያዘጋጁት።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመዝየ 15/2015 ኽምጠ ዊከ ጋዜጠ
Next article“ዕድገታችን የሚለካው ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ በምናደርገው መዋቅራዊ ለውጥ ነው” ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ