
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በዛሬው እለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የአግሮ ኢንዱስትሪና ምግብና ምግብነክ የሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።
ከዚህ ውስጥም 1 ነጥብ 15 ቢሊየን ዶላር የምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም የግብርና ማቀነባበሪያ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ መቻሉን ነው የገለጹት።
አንዳንዶቹን የምግብና ምግብነክ ምርቶች ከውጭ ሀገራት የሚገቡትን ከመተካት ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉንም አስረድተዋል።በተለይም ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ በአንድ ወር ብቻ እስከ 200 ሺህ ዶላር ለማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በዚህም በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ይጠይቁ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የምንዛሬ ወጪ ማዳን መቻሉን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።
በወጪ ምርት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የጨርቃጨርቅ ዘርፉ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ የምግብና ምግብነክ ዘርፉም የተሻለ ገቢ እያስገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተደረገው ጥረትም የተሳካ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥ ለማምረት በመቻሉም የ60 ሚሊየን ብር ግብይት መፈጸሙን ተናግረዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው፤ በቀጣይም ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!