“143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

53
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።
በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከሀገር ውስጥ 18 ቢሊየን ብር ከውጭ ደግሞ 125 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 እና በዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት የባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍላጎት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ፥ አሁን ላይ ጥሩ መሻሻሎች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 67 አዳዲስ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሃገር ውስጥ መጥተው መዋዕለ- ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለመሰማራት ሰፊ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 143 ቢሊየን ብር ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት።
በዘርፉ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪን ለማበረታታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፤ ግንባታቸው ተጠናቆ ባለሃብቶች ሳይገቡባቸው የቆዩ ኢንዱስትሪዎች እንደነበሩም አንስተዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ በተደረገው ጥረት 332 ባለሃብቶች ወደ ሥራ ለመግባት ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል እስካሁን 67 የሚሆኑት ስምምነት የተፈረመባቸው ሲሆን፤16ቱ ወደ ግንባታ መግባታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ 25ቱ ፋብሪካዎቻቸውን ሲያቋቁሙ ስምንቱ ደግሞ ወደ ማምረት ገብተዋል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ አምራች ኢንዱስትሪን ለመሳብ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሳስቧል።
ቅንጅታዊ አሠራር፣ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማሳደግ፣ ግንባታቸው ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የስኳር አቅርቦትና ፍላጎት ተመጣጣኝ አለመሆን፣ የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል ሥራ መቋረጥ እና ተመጣጣኝ የኢንዱስትሪ ስርጭት በሀገሪቱ አለመኖሩን በሚመለከት ከምክር ቤቱ የቀረቡት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ቅንጅታዊ አሠራርን በሚመለከት “በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ባለፉት 9 ወራት በሁሉም ክልሎች በተፈጠሩ መድረኮች ለ27 ሺህ ዜጎች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አስፈላጊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሠራቱን፤ እንዲሁም በኮቪድ እና በተለያዩ የጸጥታ ችግሮች ሥራ አቁመው የነበሩ 352 ኢንዱስትሪዎችም ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ተቋማት የደንብ ልብስን በሀገር ውስጥ በማምረትም ለ15 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠር መቻሉንም አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በርካታ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለኃብቶች ወደ አምራች ዘርፉ ለመግባት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸው፤ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተመጣጣኝ የኢንዱስትሪ ስርጭት ይኖር ዘንድ በየደረጃው ያሉ አመራሮች በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸውና ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሼዶች በኮቪድ እና በአግዋ ጫና የተነሳ ሥራ ላይ አለመሆናቸውንና በቀጣይ ግን ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ መሆኑን አስራድተዋል፡፡
የስኳር ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግባቸው መቋቋማቸውን፣ የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከልን ሥራ ለማስጀመር ደግሞ 850 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 2/2015 ዓ.ም ባለው “የኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖ በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጥራት ያላቸው አዳዲስ ምርቶች፣ የፈጠራ ውጤቶች እና የሀገራችንን የማምረት አቅም የሚያሳዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ሚንስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ ሀገሮች የሚያደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ ጀመሩ።
Next articleበዘጠኝ ወራት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።