
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአራት የአፍሪካ ሀገሮች የሚያደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ ጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታንዛኒያ ኮሞሮስ ቡሩንዲና ዩጋንዳ የሚያደርጉትን ጉብኝት ለመጀመር ታንዛኒያ ገብተዋል።
አቶ ደመቀ ከታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳሚያ ሳሉሁ ጋር የህንድ ውቅያኖስ ከተማ በሆነችው በዛንዚባር ዛሬ ሚያዝያ16/2015 በሁለትዮሽና አከባብያዊ ጉዳዮች ተነጋግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ጋር ላላት ግኑኝነት ትኩረት እንደምትሰጥ በመግለፅ ግኑኝነቱ በኢኮኖሚው መሰክ እንዲጠናከር እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
የታንዛኒያ ፕሬዝዳንንት ሳሚያ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግኑኝነት በተለይም በአቭዬሽንና ቱሪዝም እንዲሁም በባህል እንዲጠናከር ፍላጎቷ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በመተግበር ሰላምን ማፅናት እንደሚፈልግ አቶ ደመቀ ተናግረዋል።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በውይይት እልባት እንዲያገኝ በመጠየቅ የአረብ ሊግ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
በሱዳን ያለው ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ደመቀ ተናግረዋል።
የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት አገራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈንና ለማፅናት የሚያደርገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።
የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ከመግባባት የተደረሰ ሲሆን ታንዛኒያ ውስጥ በአዘዋዋሪዎች ተታለው በቁጥጥር ስር የሚገኙ ዜጎቻችን ተገቢው አያያዝ እንዲደረግለቸው አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።
በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ 2500 ዜጎቻችንን ባለፉት ወራት የመለሰ ሲሆን ቀሪዎቹንም ለሀገራቸው እንደሚበቁ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!