
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ምዕራብ ጎንደር አቅጣጫ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንን ከጎረቤት ሀገር እና ከጎረቤት ክልል የሚያዋስነው ሽንጠ ረጅሙ የተከዜ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ ይፈስሳል፡፡ ተከዜ ከታሪካዊ እና ከተፈጥሯዊ ድንበርነቱ ባሻገር ለበርሃዋ ገነት የዞኑ ርዕሰ ከተማ ሁመራ ሌላ የውበት ጉልላት እና ሞገሷ ነው፡፡ ከተከዜ ወንዝ የሚነሳው ነፋሻማ አየር በበረታ ሙቀት ለምትገረፈው ተናፋቂ የድንበር ዳር ከተማ ፋታ እና እስትንፋስ የሚሰጥ ገጸ በረከቷ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
ከኤርትራዊቷ የኦማሂጀር ከተማ አሻጋሪ፣ ከተከዜ ወንዝ ዳርቻ እና ከሁመራ ከተማ ቅርብ እርቀት የተዘረጋው ሰፊ እና ለም መሬት ለመስኖ ልማት እጅ የሰጠ የምርታማነት አውድማ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይኽንን በረከት የተረዳ እና የተጠቀመበት ያለ አይመስልም ነበር፡፡ በቅርቡ በአካባቢው የሰፈነውን ሠላም ተከትሎ ተስፋ ሰጭ የመስኖ ልማት ትሩፋቶች በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በቃፍቲያ ሁመራ ወረዳ የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚለማው የመስኖ ማሳ በቂ ማሳያ ነው፡፡
ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በቂ የውኃ አቅርቦት እና ማምረት የሚችል የሰው ኃይል በበቂ ያላት ሀገር ሽንኩርት ከጎረቤት ሀገራት የምታስገባበት ምንም ምክንያት መኖር የለበትም ያሉን በአካባቢው በመሰኖ ልማት የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አዘዘው ሰለሞን ናቸው፡፡ ዕቅዳቸውም በቅርብ ጊዜ ሽንኩርትን ከሀገራዊ ፍጆታ ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሆነ አጫውተውናል፡፡
የተከዜ ወንዝን ተከትሎ የተዘረጋው ሰፊ እና ለም መሬት ለመስኖ ልማት ምቹ ነው የሚሉት አቶ አዘዘው በተለያዩ ችግሮች እስካሁን ድረስ አልተጠቀምንበትም ነበር ይላሉ፡፡ ይኽንን የልምድ ችግር ሰብሮ በመግባት ለሌሎች ባለሃብቶች እና አልሚዎች አርዓያ ለመሆን በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርትን በመስኖ እያለማን ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይ ዓመታትም ዘርፉን አጠናክረው በሽንኩርት ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነት መፍጠር እንችላለን ነው ያሉት፡፡
በምርት ቅድመ ትንበያ መሰረት ከአንድ ሄክታር እስከ 300 ኩንታል ሽንኩርት እንደምናገኝ ተስፋ አድርገናል የሚሉት አቶ አዘዘው የሽንኩርት አብዮት እናመጣለን ነው ያሉት፡፡ ቀይ ሽንኩርትን ከውጭ ማስገባትን ታሪክ በማድረግ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንጀምራለን ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ለውጡን በማየት ብቻ በስፋት ለመሰማራት በቂ ምክንያት ይሆነዋል፤ ይኽንንም ለማሳየት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በቃፍቲያ ሁመራ ወረዳ በ2014/15 የምርት ዘመን 2 ሺህ 200 ሄክታር በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉን የቃፍቲያ ሁመራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ልማት ባለሙያ ወይዘሮ አታሌ ሲሳይ እስካሁን ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው ብለዋል፡፡ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ በመስኖ እየለማ ነው ያሉት ባለሙያዋ ከዚህ ውስጥ 890 ሄክታሩ መሬት በሽንኩርት የተሸፈነ ነው ይላሉ፡፡
በወረዳው ሰፊ እና ለመስኖ ልማት የሚውል ለም መሬት በብዛት አለ የሚሉት ወይዘሮ አታሌ ተከዜን ጨምሮ በርካታ የውኃ አቅም ያላቸው ጸጋዎችም አሉ፡፡ በቀጣይም ተሞክሮዎችን በማስፋት እስከ 8 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እና በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይ ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ2014/15 የምርት ዘመን 6 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የነገሩን ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ እንዳልካቸው አስፋው ናቸው፡፡ ይኽ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም 4 ሺህ 200 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ እንደሆነ ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ከ40 በላይ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች አሉ ያሉት አቶ እንዳልካቸው እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ግን ከ10 አይበልጡም ነው ያሉት፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ ቀሪዎቹን ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ወደ ሥራ እንዲያስገባቸው ተጠይቋል ተብሏል፡፡ እነዚህ የውኃ ጉድጓዶች ለሥራ ዝግጁ ሲሆኑም በዞኑ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ቡድን መሪው ነግረውናል፡፡
እንደ አቶ እንዳልካቸው ገለጻ በዞኑ 1 ሺህ 250 ሄክታር መሬት በመስኖ ሽንኩርት ልማት ተሸፍኗል፡፡ በቅድመ ምርት ግምገማ ሂደትም ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ሽንኩርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!