አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን የሚቀርፍ የትምህርት ክፍል በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ሊሰጥ መኾኑ ተገለጸ።

93
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን የሚቀርፍ የትምህርት ክፍል በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ሊሰጥ መኾኑ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከሀገሪቱ 14 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በሚከፈተው የትምህርት አይነት ዙሪያ በባሕርዳር ከተማ ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ክልሉ አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግር በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት መርሐ ግብር ተካትቶ እንዲሰጥ መደረጉ የችግሩን ምንነት እና ለምላሹ እንዴት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ዕውቀትና ክህሎት ለመያዝ ያስችላል ብለዋል። ይህም ዘላቂ ፣ በዕውቀት የሚመራ እና የተስተካከለ የምግብ ሥርዓት ለማበጀት ይጠቅማል ነው ያሉት።
ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የሥርዓተ ምግብ ችግር መከሰቱን ገልጸዋል። አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግር በተለይም በተፈናቃዮች አካባቢ ተለይተው ከተያዙ አስር የጤና ስጋቶች ውስጥ የመጀመሪያው ስለመኾኑም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
የሥርዓተ ምግብ ችግር የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዩኒቨርሲቲዎች እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት ጋርም በመተባበር ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ስለመኾኑም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በኦክስፎርድ ፓሊሲ የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ ክስተቶች አስተባባሪ ዶክተር አያና የኔአባት በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተፈጠሩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሥርዓተ ምግብ ቀውስ ሲደርስ ተመልክተናል ብለዋል። ይህንን ተከትሎም የእናቶች እና ሕፃናት ሕይወት አልፏል ነው ያሉት።
“የምግብ እጥረት በምግብ እጦት ብቻ ሳይኾን ምግብ እያለም በግንዛቤ ክፍተት ይፈጠራል” ያሉት ዶክተር አያና ዩኒቨርሲቲዎች ኅብረተሰቡ በእጁ ያለውን ምግብ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ዕውቀት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
ዶክተር አያና አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግር ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የተዘጋጀ እና ከተከሰተ በኋላም በፍጥነት ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል። ስለዚህ በመስኩ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ማፍራት ግድ ይላል ነው ያሉት።
ሥርዓተ ምግብን በተመለከተ አሁን ላይ በሀገሪቱ 14 ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት የሚሰጥ ቢኾንም አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን የተመለከተ ትምህርት ግን ተካትቶ እየተሰጠ እንዳልኾነም አመላክተዋል።
የተመረጡ 14 ዩኒቨርሲቲዎች በፊት ከሚሰጡት የሥርዓተ ምግብ ትምህርት ውስጥ አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን የተመለከተ ሌላ ዲፓርትመንት ከፍተው እንዲሠሩም ይደረጋል ነው ያሉት። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ የልሕቀት ማዕከል በመኾን እንዲያገለግል መመረጡንም ተናግረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ወክለው የተገኙት ዶክተር አስማማው አጥናፉ ዩኒቨርሲቲው በኅብረተሰብ ጤናው ዘርፍ የካበተ ልምድ እንዳለው ጠቅሰዋል። ዩኒቨርሲቲው አጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመቅረፍ ለሚከፈተው የትምህርት ክፍል የልሕቀት ማዕከል ቢኾንም ትምህርቱን ከሚሰጡ አስራ አራቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በማዕከሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ መደበኛ ትምህርት እና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ የሚስተዋለውን የሥርዓተ ምግብ ችግር ለመቅረፍ ይሠራል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚኾን ነው” ማይክ ሐመር
Next article“ከሀገራዊ ፍጆታ ባሻገር ቀይ ሽንኩርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል” የቃፍቲያ ሁመራ ወረዳ አርሶ አደሮች