“ኢትዮጵያ የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚኾን ነው” ማይክ ሐመር

155
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚኾን ነው ሲሉ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ተናገሩ።
አሜሪካ ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቀጣይ የሚጠበቅባትን ድጋፍ እንደምታደርግም ልዩ መልዕክተኛው አረጋግጠዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ‘ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና’ በሚል መሪ ሃሳብ የዕውቅና እና ምሥጋና መርሐግብር ትላንት በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ለኢዜአ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በፕሪቶሪያ የተደረሰው ሥምምነት አሜሪካ በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የተካሄደው ይኸው የሰላም ሥምምነት አሁን ላይ እዚህ በመድረሱ አሜሪካ የኢትዮጵያ አጋር ሀገር እንደመኾኗ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
ሥምምነቱ “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በማበጀት ረገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቀጣይ ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑ አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የጀመረችው የመልሶ ግንባታ ሥራ እና የሽግግር ፍትህን የማረጋገጥ ሂደትንም አሜሪካ ድጋፏን እንደምታጠናክር ተናግረዋል።
ይህንንም በተመለከተ ከመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ውይይት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ሁለት ዓመት የቆየችበትን ጦርነት በሰላም ሥምምነት የቋጨችበት መንገድ ለሌሎች ሀገራትም አርዓያነት ያለው ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ጦርነት የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ውጭ ሌላ ዓላማ እንደሌለው በመገንዘብ ግጭቱን በማቆም ወደ ውይይት ሊመጡ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜሪካም ከአፍሪካ ኅብረትና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ከመሰሉ ተቋማት ጋር በመኾን ሱዳን ካጋጠማት ችግር እንድትወጣ ድጋፏን እንደምታደርግ ነው ያረጋገጡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስፖርት ዜና ባሕር ዳር: ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ)
Next articleአጣዳፊ የሥርዓተ ምግብ ችግርን የሚቀርፍ የትምህርት ክፍል በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ሊሰጥ መኾኑ ተገለጸ።