“ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመታትን መወያየት ይበልጣል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

81

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጦርነት ይብቃ፤ ሠላም እናጽና በሚል መሪ ሐሳብ የምሥጋና እና የዕውቅና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በዕውቅና እና ምሥጋና መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠብ አቁሞ ሠላም ለመፍጠር በቂ ያልሆነ ምክንያት ትክክለኛ ያልሆነ ጊዜ የለም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከነበረችበት ጨለማ ወጥታ ወደሚገባት ብርሃን ለመሻገር ፈቅዳ የጀመረችበት ጊዜ ዛሬ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበዛ ሠላም አጭር ጊዜ የሚከሰት ጦርነት ተፈጥሯዊ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ይኽ የተለመደ አልነበረም ብለዋል፡፡
“ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመታትን መወያየት ይበልጣል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጥላቻ ጥፋት፤ ከውይይት ደግሞ መፍትሔ እና ብልሃት ይፈልቃል ነው ያሉት፡፡

ይቅርታ ማስቀረት ነው፤ እርቅ ግን ማረም ጭምር ይሆናል ያሉት ዶክተር ዐቢይ ዛሬ ይቅርታም እርቅም በመሆኑ ጥላቻን፣ መገፋፋትን፣ ግጭትን እና ብሽሽቅን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ያለፈ ስህተትንም ማረም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት የተፈጠሩ ሰባራዎችን ማከም እና ማረም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በጦርነት ልምድ ብቻ ሳይሆን በጀግንነትም የምትታውቅ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኽንን በሠላም ማረጋገጥ እና መድገም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለሠላም ከተጓዝነው በላይ መጓዝ ስለሚያስፈልግ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች ተሞክሮውን እንዲወስዱ እና እንዲያስቀጥሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ከዲሞፍተር ይልቅ አብዝታ ሞፈር እንደምትፈልግ ገልጸው ሁሉም ለልማት እና ለሠላም እንዲሠራ ተማጽነዋል፡፡
በውጊያ የላቁ፣ በጀብድ የደመቁ እና በሀገር ፍቅር ያሸበረቁ ብቁ ወታደሮች ስላሉን ዲሞፍተሩን ለእነርሱ መተው ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው “ሲታረቁ ከሆድ፤ ሲታጠቡ ከክንድ” ይላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትናንት ከልባችን ተዋግተናል ዛሬ ግን ከልባችን ለእርቅ እና ሠላም እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous article“ሰላምን የሚሹ የዓለም ታላላቅ ሕዝቦች ታላቅ ከሆናችሁት ከእናንተ ከኢትዮጵያዊያን መማር ይችላሉ” ሙሳ ፋቂ ማሕማት
Next articleጽኑ ብርሃን