
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጦርነት ይብቃ፤ ሠላምን እናጽና በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ አፍሪካው የፕሪቶሪያ ሠላም ስምምነት የተሳተፉ አካላት ሽኝት እና ምሥጋና በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በወርሃ ጥቅምት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተካሄደ፡፡ ኢትዮጵያ ደግማ እና ደጋግማ አፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ያሻቸዋል እንጂ የሌሎችን ጣልቃ ገብነት እና የመሳሪያ መማዘዝ አያስፈልጋትም ብትልም ይህ ሳይሆን ቀርቶ የከፋ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ያስተናገደ ግጭት ተስተናገደ፡፡
በጦርነቱ ከጉዳት የዘለለ ዘላቂ ሰላም እና መፍትሔ ማምጣት እንደማይቻል ያረጋገጡት የጦርነቱ ባለቤቶች ዘግይተውም ቢሆን በመጨረሻ ለሰላም በራቸውን ክፍት አደረጉ፡፡ ሠላምን አጥብቆ የሚሻ እና ጦርነትን የሚጠላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረበውን የሰላም ጥሪ ያለቅድመ ሁኔታ ተቀበለና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በጥቅምት የመጀመሪያው የሰላም ሥምምነት እውን ሆነ፡፡
ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መሪነት የተጀመረው የሠላም ሥምምነት የሠላም ድባብን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አሰፈነ፡፡ ዛሬ ደግሞ የዚህ ሰላም ሥምምነት ተዋናዮችን ለማመስገን እና ለመሸኘት በአዲስ አበባ የወዳጅነት አደባባይ በሰላም ሥምምነቱ የተሳተፉት ሁሉ ተሰባስበዋል፡፡
በልዩ መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሕመት “ሠላምን የሚሹ የዓለም ታላላቅ ሕዝቦች ታላቅ ከሆናችሁት ከእናንተ ከኢትዮጵያዊያን መማር ይችላሉ” ብለዋል፡፡ አፍሪካውያን ካለፉ ሥህተቶቻችን በሁለት መንገድ ተምረናል ያሉት ሊቀመንበሩ ከጦርነቱ ውድመትን ከሰላም ስምምነቱ ደግሞ ዘላቂ ሰላምን እና አማራጭ መፍትሔዎችን አይተናል ነው ያሉት፡፡
አፍሪካ ከመሰል ግጭቶች ልትጸዳ ይገባል ያሉት ሊቀመንበሩ ሱዳናውያን ወንድሞቻችን ትምህርት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ዕውቁን የደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ንግግር በመዋስ ሊቀመንበሩ በመጨረሻም “እርቅ ከሕግ ማዕቀፍ በላይ በሰዎች ልብ እና አዕምሮ ውስጥ መንፈሳዊ ሂደትን የሚፈልግ ተግባር ነው” በማለት የሰላም ሥምምነቱ እንዲጸና ሁሉም ኅይሎች ከልብ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!