ሰላሳ ስምንት ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራና ሥልጠና መምሪያ ገለጸ። አዘዋዋሪዎቹ ከ4 እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ1 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በገንዘብ መቀጣታቸውን መምሪያው ገልጿል።

66

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ለከፋ እንግልትና ጉዳት እየዳረገ ለሀገርም ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳይ ነው። ከሃገር ርቆ ለመሰደድ የተለያዩ ገፊ እና ሳቢ ምክንያቶች አሉ። ዜጎች ሃገራቸውን ለቀው ከተሰደዱ በኃላ ሕሊናንና ስብዕናን በሚፈትኑ ሁኔታዎች ውስጥ መኖር ፣ መታሰር ፣ በግፍ መንገላታት አለፍ ሲልም ህይዎትን እስከማጣት ይደርሳሉ።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በክልላችን ፣ በሃገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ጉዳይ ኾኗል። በምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራና ሥልጠና መምሪያ የሥራ ሥምሪት ማስፋፊያ ቡድን መሪ ወልዴ ገብሬ በዞኑ በምድረ ገነት፣ በአብርሃ ጅራ፣ በቋራ፣ በመተማ እና በቲሃ በኩል ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ባለፉት ወራት ከ8 መቶ በላይ ሰዎች ተይዘው በመተማ በሚገኘው የስደተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ መጡበት የመመለስ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ቡድን መሪው እንዳሉት ስደተኞቹ በአብዛኛው ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና ከኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ተነስተው የመጡ ናቸው። በሕገ ወጥ መንገድ የሚዘዋወሩት ግለሰቦችም የአስገድዶ መደፈር፣ ድብደባ እና የሥነ ልቦና ችግር እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከሱዳን መንግሥት ጋር በየጊዜው ውይይቶች ቢካሄድም ከጉዳዩ ውስብስብነት እና ዞኑ ከሱዳን ጋር ካለው የወሰን ሰፋት አኳያ ዝውውሩን በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።
ይህም በዞኑ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ነው ኮማንደር አሰፋ የገለጹት።
ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ 44 ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ቡድን መሪው ነግረውናል።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ከባድ መኾኑን የገለጹት ቡድን መሪው በዝውውሩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ጭምር ተሳታፊ ኾነው መገኘታቸውን ነው ያነሱት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር አሰፋ ሽቤ በዞኑ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ስደተኞቹ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ዞኑ ለሥራ ከመጡ በኋላ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን የሚሻገሩት በርካቶች ናቸው። ከሃገር ከወጡ በኋላም የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደሚደርስባቸውም ገልጸዋል።
ችግሩን በጋራ ለመከላከል ከወላጅ ጀምሮ የመንግሥት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየካዛ ወንዝ በረከት!
Next article“ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያን የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ለመደገፍ ዝግጁ ናት” የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር