የካዛ ወንዝ በረከት!

80
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ገና በማለዳው የጠዋትዋ ፀሐይ ከተናፋቂ ሙቀትነት አልፋ አስፈሪ ንዳድ ፈጥራለች፡፡ ከጠዋቱ ሦሥት ሰዓት በፊት 32 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የደረሰው የአካባቢው የሙቀት መጠን ለነዋሪዎቹ ብዙም የሚያስገርም አይመስልም፡፡ አንዳንዶቹ በግንባራቸው የሚንቆረቆረውን ላብ ተላምደውት መጥረግ እንኳን ትዝ አይላቸውም፡፡ ከሰዎቹ ይልቅ ግመሎቹ እና ፍየሎቹ የዛፍ ጥላ እየፈለጉ ተመስገዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ቀበሌ የምትገኘው እና የካዛ ወንዝን ተንተርሳ የከተመችው የሂላብ ሰፈር ደግሞ ለንጽጽር የማይመች ሌላ ዓለም ትመስላለች፡፡
በዚያ ዝቅተኛ ቦታ ላይ የታፈነው አየር በፀሐይ ሙቀት ለምትቆላው የዓለም ገነት ቀበሌ ሌላ ረመጥ የፈጠረ ይመስላል፡፡ ከዚች ከተማ ቀመስ አነስተኛ ቀበሌ ጀርባ ምድራዊ ገነት ይኖራል ብሎ ለመገመት ቢከብድም በከተማዋ ውስጥ በብዛት የሚስተዋለው የአትክልት እና ፍራፍሬ ገበያ መድራት በአካባቢው ሌላ ጸጋ ለመኖሩ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ በየሱቁ በር የተቀመጡት ታላላቅ የብረት ሚዛኖች ሥራቸው የካዛ ወንዝ በረከትን ለሽያጭ እና ግዥ መመዘን ነው፡፡ በአካባቢው ውር ውር የሚሉት ሽንጣም ሽንጣም የጭነት መኪኖች ደግሞ የሂላብን ጸጋ ወደ መሃል ሀገር ያሸጋግራሉ፡፡
የካዛ ወንዝ በሙቀት ብዛት የሚጠበሰውን አካባቢ ከማረስረስ ባለፈ በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የወልቃይት እና ጠገዴ ወረዳዎች ተፈጥሯዊ ድንበር ነው፡፡ ወዲህ ማዶ ጠገዴ ወዲያ ማዶ ወልቃይት፡፡ ከወዲያ ማዶም ከወዲህ ማዶም ፍየሎቻቸውን እና ከብቶቻቸውን ውኃ ለማጠጣት የሚመጡ ወጣቶች በካዛ ወንዝ ውስጥ እየዋኙ ንዳዱን በውኃ ሲያስታግሱ መመልከት እፎይታን ይሰጣል፡፡ እግረ መንገዳቸውን ዓሣ እያሰገሩ ውኃው ውስጥ ረጂም ጊዜ የሚቆዩት ታዳጊዎች የካዛ ወንዝን አመስጋኞች ይመስላሉ፡፡
በጠገዴ ወረዳ ዓለም ገነት ቀበሌ ከቀበሌዋ ማዕከል በግምት ከ15 ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ የምትገኘው ሂላብ ሰፈር የካዛ ወንዝን ተንተርሳ አረንጓዴ ለብሳለች፡፡ በአካባቢው ካሉ ዛፎች ላይ ተንጠልጥለው የሚዘምሩት አዕዋፍት በካዛ ወንዝ ውስጥ ለሚንቦጫረቁት ወጣቶች ሌላ ሕብረ ዝማሬ የፈጠረላቸው ይመስላል፡፡ ሂላብ፦ ቲማቲም፣ ሙዝ፣ ሎሚ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ጥቅል ጎመን እና ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችን የሚያለሙ ነዋሪዎቿ ከጎንደር እስከ ሁመራ፣ ከዳንሻ እስከ አዲስ አበባ በመኪና እያስጫኑ ሀገሬውን ይመግባሉ እነርሱም ጥሪት ይቋጥራሉ፡፡
አርሶ አደር ላቀው ልጃለም እና አርሶ አደር ንጉሴ ግርማ በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ ዓለም ገነት ቀበሌ ሂላብ ሰፈር ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አርሶ አደሮቹ የካዛ ወንዝን ተከትሎ በመስኖ ልማት ከሚያለሙ 150 የሂላብ ጎጥ አርሶ አደሮች መካከል ናቸው፡፡ ለምድሪቷ የተቸረ ጸጋ የሚሉትን የካዛ ወንዝን ተጠቅመው ዓመቱን ሙሉ በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ ነን ይላሉ፡፡ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ መንደሪን፣ ማንጎ እና ሌሎች የቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ ሲያለሙ፤ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን እና ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እያለሙ ለገበያ እንደሚያቀርቡ አጫውተውናል፡፡
ዓመቱን ሙሉ በመስኖ አትክልትን እና ፍራፍሬን ማልማት ለአካባቢው ልምድ እየሆነ መጥቷል የሚሉት አርሶ አደሮቹ የእነርሱን ተሞክሮ ወስደው እና የካዛ ወንዝን ተከትለው 150 አርሶ አደሮች በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተዋል፡፡ የገበያ ትስስሩ እየተሻሻለ መምጣት ለመስኖ ልማቱ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ያሉት አርሶ አደሮቹ በቀጣይ ጊዜያትም በተሻለ መጠን፣ በተሻሻሉ ዝርያዎች እና ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ለማምረት እንደሚሰሩ ነግረውናል፡፡
የካዛ ወንዝን ተገን አድርገው የሚያለሙ የሂላብ ሰፈር አርሶ አደሮች ከጊዜ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ 150 ደርሷል ያሉን ደግሞ የጠገዴ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ቡድን መሪ አቶ አንጋው በላይ በወረዳው በመስኖ መልማት ከሚችለው 1 ሺህ 638 ሄክታር መሬት ውስጥ 134 ሄክታሩ በዓለም ገነት ቀበሌ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ በ94 ሄክታር ላይ የተሰማሩትን 150 አርሶ አደሮች ተሞክሮ በማስፋት ሁሉንም አካባቢ በመስኖ ለመሸፈን እየሰሩ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና የከነማ መድኃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድኃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
Next articleሰላሳ ስምንት ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራና ሥልጠና መምሪያ ገለጸ። አዘዋዋሪዎቹ ከ4 እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ1 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በገንዘብ መቀጣታቸውን መምሪያው ገልጿል።