
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድኃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድኃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ።
የመድኃኒት ግዢ ዲጂታል መደረጉ የመድኃኒት እጥረትን በማቃለልና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ መድኃኒትን ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ገዝቶ በማከማቸት የማሰራጨትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ቢሆንም በመድኃኒቶች መጋዘን ውስጥ እያሉ አልፎ አልፎ እጥረቶች የሚከሰቱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመድኃኒት ግዢ ዲጂታል መደረጉ የመድኃኒት እጥረትን በማቃለልና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
የመድኃኒት ግዢና ስርጭት በማንዋል በነበረበት ጊዜ ተደራሽ ለማድረግ እስከ 200 ቀናት ይፈጅ እንደነበር አስታውሰው ዲጂታል ከተደረገ በኋላ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ተደራሽ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም የመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና የከነማ መድኃኒት ቤቶችን በዲጂታል የመድኃኒት ግዢና ስርጭት መተግበሪያን ማስተሳሰር ተችሏል ነው ያሉት።
የመድኃኒት ክምችትና ስርጭትን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች የሚቀጥሉ መሆኑን ጠቅሰው አጋር አካላት የሚሳተፉበት ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጤና ተቋማት የመድኃኒት ክምችታቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚችሉበት የአሰራር ሥርዓት ዕውን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድኃኒቶችን ከክፍያ ነጻ በማድረግ ለተጠቃሚዎች በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮችም ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በጤና ፕሮግራም የሚካተቱ መድኃኒቶችን በማቅረብ ከ95 በመቶ በላይ የተሳካ ሥራ መከናወኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 19 የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖች መኖራቸውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!