በወረዳው በመስኖ ስንዴ ከተሸፈነው ሰብል ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዳንግላ ወረዳ አስታወቀ።

93
እንጅባራ: ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የዳንግላ ወረዳ በ29 ቀበሌዎች የተዋቀረ ወረዳ ሲሆን አብዛኛው ቀበሌዎች የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ከራስ ፍጆታ አልፎ ምርትን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ወረዳው በሰብል ልማትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ አመቺ ነው።
አርሶ አደር የሰራህ ገሰሰ እና ወይዘሮ ፋሲካ ልይህ በዳንግላ ወረዳ የምሥራቅ ዘለሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።ለረጅም ዓመታት በመስኖ በርበሬ፣ድንች፣በቆሎ፣ሽንኩርት እና ሌሎችንም ሰብሎቸች በመዝራት ተጠቃሚ እንደነበሩ ነግረውናል። አርሶ አደሮቹ ከራሳቸው የዕለት ቀለብ አልፈው ለገበያም የሚያቀርቡ እንደሆኑ ነው ያስረዱት። አርሶ አደሮቹ አሁን ላይ ደግሞ ስንዴን በመስኖ በመዝራት ተጠቃሚ መኾን እንደቻሉ ነው ያስገነዘቡት።
በቀበሌው በሞዴል አርሶ አደሮች የተጀመረው የመስኖ ሰንዴ ልማት አሁን ላይ ሁሉም አርሶ አደር እንዲያለማው ማድረግ ተችሏል። አርሶ አደሮቹ የስንዴው ቁመና የተሻለ በመሆኑ ከፍተኛ ምርት አንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ለቀጣይም መንግሥት ለመስኖ የሚሆኑ ጀኔሬተሮችን ከአቀረበ ይበልጥ አስፍተው እንደሚያለሙ ገልጸው በወቅቱ ማዳበሪያን ጨምሮ ምርጥ ዘር እና ሌሎች ግብዓቶችም እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በዳንግላ ወረዳ የምሥራቅ ዘለሳ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሽታ ቀበሌው ከ747 ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት እንዳለው ተናግረዋል።
ኀላፊው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ድንች በመዝራት ውጤታማ ያልነበረችው ማሳም ቀበሌን ጨምሮ በበርካታ ቀበሌዎች በስንዴ ልማቱ ውጤታማ መሆን መቻሉን ነው የገለጹት። አሚኮ የተገኘባት ማሳም ቀበሌም በስንዴ ልማቱ ውጤታማ መሆኗን ታዝበናል።
በዘንድሮ የበጋ ወቅት ከ108 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ የለማ ሲሆን ከ5 ሺህ በላይ ኩንታል ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል። አቶ ሞላ ቀበሌው ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን በመስኖ ያለማ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ የተለያዩ ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ምርቱ እስከሚሰበሰብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ድጋፍና ከትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። ለቀጣይም ስንዴን በመስኖ ማልማቱን የበለጠ አስፍተው እንደሚሰሩም ኀላፊው ነግረውናል።
የዳንግላ ወረዳ ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መልማት የሚችል መሬት መኖሩን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ኀይለኢየሱስ ማለደ ናቸው። ወረዳው የበርካታ ትላልቅ ወንዞች ባለቤት ቢሆንም ያለውን አቅም አሟጦ የመጠቀም ውስንነት መኖሩን የገለጹት አቶ ኀይለእየሱስ፤በዘንድሮ የበጋ ወቅት 1 ሺህ 300 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 2 ሺህ 100 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ብቻ መሸፈን እንደተቻለ ነው የሚናገሩት። ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
ከ29ኙ ቀበሌዎች 18 ቀበሌዎች ስንዴን ማልማት ጀምረዋል ያሉት ምክትል ኀላፊው እንደምሥራቅ ዘለሳ ቀበሌ የአመለካከት ችግሮችን ቀርፈው ስንዴ በመስኖ እንዲያለሙ ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ሁሉም ቀበሌዎች ስንዴን በበጋ ማልማት እንዲችሉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አርሶ አደሮች የጠየቁትን የጄኔሬተር እና የግብዓት አቅርቦት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እና በጋራ እየሠሩ በመሆኑ ችግሩ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleበመንግሥት ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና የከነማ መድኃኒት ቤቶች ዲጂታላይዝ የመድኃኒት ስርጭት አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።